
ባሕር ዳር: ግንቦት 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ምሥራቅ ዕዝ የተጣለበትን ሕገ መንግሥታዊ ተልዕኮ ለመወጣት ያደረጋቸው ስምሪቶች የሕዝብን የሰላም እና የልማት ፍላጎት ማሳካታቸውን በሀገር መከላከያ ሠራዊት የምሥራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ ገልጸዋል።
ሌተናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ እንደተናገሩት ምሥራቅ ዕዝ በተሰማራባቸው በሰሜን ጎጃም፣ በምዕራብ ጎጃም፣ በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዞን እና በደቡብ ጎንደር ዞን በጠላት ላይ ጠንካራ ምት በማሳረፍ ጽንፈኞችን እና ባንዳዎችን የደመሰሰ ሲኾን ሕገ መንግሥቱን በአስተማማኝ ሁኔታ በመጠበቅም የሕዝብ አለኝታነቱን በተግባር ያስመሰከረ ዕዝ ነው ብለዋል።
በመከላከያ ሠራዊታችን እና በክልሉ የጸጥታ ኀይል የተቀናጀ ስምሪት በጽንፈኛው ቡድን ላይ በደረሰው ጠንካራ ምት ምክንያት አሁን ላይ የሠራዊቱን ክንድ መቋቋም አቅቶት በየጉድጓዱ ተደብቆ “አለሁ” ለማለት ብቻ ብቅ ጥልቅ እያለ ነው ብለዋል።
ተላላኪው ጽንፈኛ ቡድን ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር ቅንጅት በመፍጠር ኢትዮጵያን መንግሥት አልባ ለማድረግ ቢፍጨረጨርም በልማት ወዳዱ ማኅበረሰብ እና በጸጥታ ኀይሉ ጀብድ ዓላማው ሙሉ በሙሉ ሊከሽፍ ችሏል ነው ያሉት።
በመኾኑም ይህንን ተላላኪ ኀይል ከተደበቀበት አውጥቶ ለመደምሰስ በሚደረገው የሕግ ማስከበር ግዳጅ ሕዝቡ የተለመደውን ጥቆማ በመስጠት ኀላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት በአማራ ክልል በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ ድረስ ሳኅሉ (ዶ.ር) የምሥራቅ ዕዝ እና የክልሉ የጸጥታ ኀይል በሠሩት ሥራ ክልሉ ወደ ቀደመ ሰላሙ እየተመለሠ መሆኑን ገልጸዋል።
ማኅበረሰቡም በሠራዊቱ ላይ የነበረውን የተዛባ አመለካከት በማስወገድ የጽንፈኛው ፕሮፖጋንዳ ሳይበግረው የአካባቢውን የልማት ሥራዎች በስፋት እያስቀጠለ እንደሚገኝ ዶክተር ድረስ ገልጸዋል።
በተካሄደው የጋራ ውይይት መድረክ ላይ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)፣ ከፍተኛ መሪዎችና የምሥራቅ ዕዝ መሪዎች መገኘታቸውን መሥራቅ እዝ የላከው መረጃ አመላክቷል።
#አሚኮ_ዜና #ጽንፈኛን_ማጽዳት #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
