ሰላም በጋራ ጥረት እና በትብብር የሚረጋገጥ የጋራ እሴት ነው።

1
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ 1 ሺህ 447ኛው የዒድ አል-አደሃ (አረፋ) በዓል ያለምንም የጸጥታ ስጋት በሰላም እንዲጠናቀቅ ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን አስታውቋል።
የአረፋ በዓል የእስልምና እምነት ተከታዮች እርስ በርስ የሚተሳሰቡበት፣ የሚከባበሩበት፣ የተቸገሩ ወገኖችን የሚረዱበት፤ አንድነት እና ፍቅር ጎልቶ የሚታይበት ታላቅ ሃይማኖታዊ በዓል መኾኑን ጠቅላይ መምሪያው ገልጿል።
ከሃይማኖታዊ በዓሉ ባሻገር መልካም እሴቶች ተጠብቀው በዓሉ በሰላም እና በደስታ እንዲከበር የክልሉ የጸጥታ ኃይል ሌት ከቀን በቁርጠኝነት እየሠራ መኾኑንም መረጃው አመላክቷል።
የጸጥታ መዋቅሩ በዓሉ ፍጹም ሰላማዊ በኾነ መንገድ እንዲከበር ልዩ ትኩረት በመስጠት ሰፊ ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ መጠናቀቁ ነው የተገለጸው።
በበዓሉ ቀን ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ በሚከበርባቸው መስጂዶች፤ አደባባዮች እና የሕዝብ መዝናኛ ቦታዎች ላይ በቂ የጸጥታ ኃይል እና የሎጀስቲክስ ስምሪት እንደሚደረግ ነው የተመላከተው።
ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ያለምንም ስጋት በዓሉን እንዲያከብር ከሌሎች የጸጥታ አካላት እና ከበዓሉ አሥተባባሪ ኮሚቴዎች ጋር የጠበቀ የጋራ ቅንጅት እንደተፈጠረም ተነስቷል።
“ሰላም በጋራ ጥረት እና በትብብር የሚረጋገጥ የጋራ እሴት ነው” ያለው ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያው በዓሉ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ይዘቱን ሳይለቅ ፍጹም ሰላማዊ እና ድምቀት ያለው ኾኖ እንዲከበር ማኅበረሰቡ የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርቧል።
አጠራጣሪ ነገሮችን፤ ጸጉረ-ልውጥ ሰዎችን እና የሰላም መደፍረስ ምልክቶችን ሲያስተውል በአቅራቢያ ለሚገኙ የጸጥታ አካላት በአስቸኳይ በመጠቆም ዜጋዊ ኀላፊነቱን እንዲወጣም አሳስቧል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
Previous articleሰላም ለማረጋገጥ በቅንጅት መሥራት ይገባል።
Next articleበዳባት ወረዳ እና በዳባት ከተማ አሥተዳደር ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገባቸው ፕሮጀክቶች ተመረቁ።