
ደባርቅ፡ ግንቦት 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በዳባት ወረዳ እና በከተማ አሥተዳደሩ ከ 1ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገባቸው በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በመንገድ፣ በንጹህ መጠጥ ውኃ እና በሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፎች ላይ ያተኮሩ 132 ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው ተመርቀዋል።
ፕሮጀክቶቹ በመንግሥት በጀት፣ በኅብረተሰቡ ተሳትፎ እና ከአጋር ድርጅቶች በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ነው የተገነቡት።
በምረቃ መርሐግብሩ የሀገር መከላከያ ሠራዊት መሪዎች፣ የክልል እና የዞን የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የስደተኞች ተጽዕኖ ምላሽ የልማት ፕሮጀክት ዋና አስተባባሪ መንግሥቱ ድልነሳው በአካባቢው የሚገኙትን ዓለም አቀፍ ስደተኞችን መሠረት አድርገው በ36 ቀበሌዎች ከ220 ሺህ በላይ ማኅበረሰቦችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ሦሥት ዓመታት የተለያዩ የልማት ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል። በዚህም 82 ፕሮጀክቶችን አጠናቀው ወደ አገልግሎት ማስገባታቸውንም አክለዋል።
ፕሮጀክቱ በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በመንገድ፣ በንጹህ መጠጥ ውኃ እና በሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፎች ተግባራዊ ለውጥ ያመጡ ሥራዎችን ማከናዎኑን አብራርተዋል።
የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ዲያቆን ሸጋው ውቤ የፕሮጀክቶች ምረቃ የልማት ሥራዎችን በማጠናቀቅ በኩል የተሻለ ተሞክሮ የሚወሰድበት መኾኑንም ገልጸዋል።
የተመረቁ ፕሮጀክቶች የማኅበረሰቡን የልማት ጥያቄ የሚፈቱ እና ተደራሽ አገልግሎት ለመስጠት የሚያግዙ ናቸው ብለዋል።
በጸጥታ ችግር ምክንያት የልማት ሥራዎቹ እንዳይቆሙ ማኅበረሰቡ በባለቤትነት ስሜት ከመንግሥት ጎን ተሰልፎ በጋራ ሢሠራ መቆየቱንም ገልጸዋል።
የዳባት ወረዳ አሥተዳዳሪ መርሻ ወረታ በወረዳው ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ 79 ፕሮጀክቶች ተገንብተው መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።
ማኅበረሰቡን በማሳተፍ ፕሮጀክቶቹን በዕኔነት ስሜት እንዲጠብቅ ለማስቻል የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ እና ውይይት መካሄዱን ገልጸዋል።
የዳባት ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ሃብትሼት ሞገስ ከ370 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ 53 ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ከፍት መኾናቸውን ተናግረዋል።
በተጨማሪም የአካባቢ ጥበቃ እና የኅብረተሰብ ኑሮ ማሻሻያ ሥራዎች በሰፊው መከናዎናቸውንም ገልጸዋል።
ማኅበረሰቡ ለፕሮጀክቶቹ መሳካት ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸው በቀጣይም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎችም የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች በሚሰጡት አገልግሎት የወረዳው የጤና፣ የትምህርት፣ የንጹህ መጠጥ ውኃን ሽፋን ያሳደጉ መኾናቸውን ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ደረጀ ደርበው
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
