ሰላም ለማረጋገጥ በቅንጅት መሥራት ይገባል።

6
ሁመራ፡ ግንቦት 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ከባለሃብቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከሃይማኖት አባቶች እና ከተጽዕኖ ፈጣሪ የዞኑ ነዋሪዎች ጋር በአካባቢው የሰላም እና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሁመራ ከተማ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
የአማራ ክልል የግብርና ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን ኀላፊ ፈንታሁን ስጦታው ሰላም እና ልማት የማይነጣጠሉ ተግባራት መኾናቸውን ተናግረዋል። በመኾኑም በመጭው የክረምት ወቅት ለሚከናወነው ሰፊ የግብርና ሥራ ቅድመ ዝግጅት ዞኑን ፍጹም ሰላም ማድረግ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው ብለዋል።
ለዚህም አርሶ አደሮች፣ ባለሃብቶች፣ መንግሥት እና የጸጥታ መዋቅሩ በቅንጅት በመሥራት አካባቢው የሚታወቅበትን ሰፊ የግብርና ልማት ውጤታማ ለማድረግ የጋራ ርብርብ ማድረግ አስፈላጊ መኾኑን አንስተዋል።
የዞኑ ምክትል አሥተዳዳሪ እና የሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ የዞኑን ቁልፍ ሥፍራዎች ተደራጅቶ በመጠበቅ ረገድ የዞኑ ባለሃብቶች የማይተካ ሚና እንዳላቸው አንስተዋል። በዚህም የጸጥታ መዋቅሩን ማገዝ እንደሚቻል ነው ኮሎኔል ደመቀ የገለጹት። የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶችም ሰላምን ከማስፈን አኳያ ግንባር ቀደም ሊኾኑ ይገባል ነው ያሉት።
የዞኑን ሰላም ለማደፍረስ በሚሞክሩ አካላት ላይ ጠንካራ እርምጃ መውሰድ የጸጥታ መዋቅሩ እና የሚመለከተው የመንግሥት አካል ኀላፊነት መኾኑንም ተናግረዋል።
አልሚ ባለሃብቶች እና የጸጥታ አካላት በትስስር እና በመተባበር መሥራት ከቻሉ የዞኑን ሰላም በዘላቂነት ማስፈን እንደሚቻልም የመድረኩ ተሳታፊ ባለሃብቶች ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ አምሳሉ አሞኘ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
Previous articleከተረጅነት ወደ ምርታማነት ለማሸጋገር የሚያስችሉ ተግባራት በትኩረት እየተሠሩ ነው።
Next articleሰላም በጋራ ጥረት እና በትብብር የሚረጋገጥ የጋራ እሴት ነው።