ከተረጅነት ወደ ምርታማነት ለማሸጋገር የሚያስችሉ ተግባራት በትኩረት እየተሠሩ ነው።

5
ባሕር ዳር: ግንቦት 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በክልሉ የሚከሰቱ አደጋዎችን ቀድሞ ለመከላከል እና ማኅበረሰቡን በራስ አቅም መልሶ ለማቋቋም ከባለ ድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል።
​የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ሰርክአዲስ አታሌ ከዚህ ቀደም የነበረው አሠራር ለአንድ አደጋ አንድ ምላሽ የመስጠት እንደነበር አስታውሰዋል።
አሁን ላይ ካለፈው ተሞክሮ በመነሳት የተሻሻለ ፖሊሲን ወደ ሥራ ማስገባት እንደተቻለም አንስተዋል።
በአሁኑ ወቅት የሚስተዋሉ የብዝኅ-አደጋዎች ሰፊ የሰው ኃይል እና ሁለንተናዊ ምላሽ የሚፈልጉ በመኾናቸው ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መሥራት ማስፈለጉን አብራርተዋል።
አደጋ ስጋትን ቀድሞ ተንብዮ በራስ አቅም መቆም የሚችል ማኅበረሰብ ለመፍጠር እየተሠራ እንደኾነም ገልጸዋል። ተቋማት በዕውቀት መር አሠራር ኅላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
​በኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጅ ኢንስቲትዩት የምዕራብ አማራ ሚቲዎሮሎጅ አገልግሎት ማዕከል የሚቲዎሮሎጅ ባለሙያ መልካሙ በላይ ማዕከሉ ዓለም አቀፍ መረጃዎችን በመሠብሠብ ሕዝቡን የማንቃት ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
ይህም በተለይ በክረምት እና በበጋ ወቅቶች የሚከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎችን ቀድሞ ለመከላከል እና የትንበያ መረጃዎችን ለፈጻሚ አካላት ቀድሞ በመስጠት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መኾኑን ነው ያነሱት።
​ከግብርና ቢሮ የመጡት የመድረኩ ተሳታፊ ዳንኤል ቁሜ ማኅበረሰቡን ከተረጅነት ወደ ምርታማነት ለማሸጋገር የሚያስችሉ የፋይናንስ እና የግብዓት አቅርቦት ሥራዎች ላይ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
ረሃብን እና አደጋን በዘላቂነት መቋቋም የሚቻልበት አሠራር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
Previous articleበአማራ ክልል 100 ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ እንደሚወስዱ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
Next articleሰላም ለማረጋገጥ በቅንጅት መሥራት ይገባል።