
ባሕር ዳር: ግንቦት 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የፊታችን ሰኔ ወር መገባደጃ ላይ የሚሰጠውን የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና በስኬት ለማስኬድ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታውቋል።
የቢሮው ምክትል ኀላፊ እየሩስ መንግሥቱ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ቢሮው ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት ቅድመ ዝግጅቱን እያጠናቀቀ ነው ብለዋል።
በዚህ የትምህርት ዘመን ላይም 99 ሺህ 897 ተማሪዎች ፈተናውን ይወስዳሉ ነው ያሉት።
በሀገር አቀፍ ደረጃ የተያዘውን ተማሪዎችን በበይነ መረብ የመፈተን ዕቅድ በክልሉ ለመተግበር ርብርብ እየተደረገ ስለመኾኑም አስረድተዋል።
በክልሉ የሚገኙ 539 ትምህርት ቤቶች የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና እንደሚያስፈትኑም ምክትል ኀላፊዋ ገልጸዋል።
ከእነዚህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 315ቱ በበይነ መረብ አማካኝነት ለተማሪዎቻቸው ፈተናውን ይሰጣሉም ብለዋል። በበይነ መረብ ተማሪዎቻቸውን ከሚያስፈትኑት መካከልም 215 ትምህርት ቤቶች በክልሉ በሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚያስፈትኑ ይኾናል ነው ያሉት።
ቀሪ 100 ትምህርት ቤቶች በራሳቸው ማዕከላት እና በአይ ሲ ቲ ማዕከላት እንደሚያስፈትኑ ነው የተናገሩት።
ቀሪዎቹ ትምህረት ቤቶች ደግሞ በተለመደው የወረቀት ፈተና አሰጣጥ ሂደት ፈተናውን እንደሚያካሂዱ ገልጸዋል።
በበይነ መረብ አማካኝነት ተማሪዎችን በስኬት ለማስፈተን ከኢትዮ ቴሌኮም እና ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በቅንጅት እየተሠራ ስለመኾኑም ምክትል ኀላፊዋ አንስተዋል።
ተፈታኝ ተማሪዎቹ ቴክኖሎጅውን እንዲለማመዱት የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል ነው ያሉት።
የበይነ መረብ ፈተና ሥርዓት ኩረጃን በማስቀረት አይነተኛ ሚና እንደሚጫወትም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ኤልያስ ፈጠነ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
