
ወልድያ: ግንቦት 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የወልድያ ከተማ ሕዝብ ለብልጽግና ፓርቲ ያለውን ድጋፍ በአደባባይ ገልጿል።
የወልድያ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዱባለ አብራሬ ወልድያ ከተማ ታታሪ ሕዝቦች ያሉባት ከተማ ናት ብለዋል።
ካሳለፍነው አኳያ ወደፊት የምናየው ልማት እና ብሩህ ተስፋ ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ባለፉት ወራት በአንድ እጅ ልማት በሌላ እጅ ሰላምን ማስከበር ላይ ኾነን ከተማችንን ከአቧራ አራግፈናል ብለዋል።
የኮሪደር ልማት፣ የሞሰብ አንድ ማዕከል፣ የገበያ አዳራሽ፣ የሕዝብ ቤተመጻሕፍት፣ የአይሲቲ ማዕከል፣ ዘመናዊ ትራንስፖርት፣ የሌማት ትሩፋት እና መሰል ልማቶች ማሳያዎች አንደኾኑም ጠቅሰዋል።
እኛ እዚህ ላይ አንቆምም ከዚህ የተሻለ ከተማ ሕዝባችን ይገባዋል ነው ያሉት።
ወልድያን ከጉስቁልና ወደ ልዕልና ለምናደርገው ጉዞ ፍላጎቱም ቁጭቱም አለን፤ ለዚህም ምርጫውን በውጤታማነት መፈጸም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍስሀ ደሳለኝ የወልድያ ሕዝብ እና መሪ ከተማዋን ዳግም ለመሞሸር አቧራዋን አራግፋችሁ ሁሉም ሰው የሚወዳት የበለጸገች ወልድያን ለመገንባት እያደረጋችሁት ላለው ትብብር አመሠግናለሁ ነው ያሉት።
ልማቱም አንድ የብልጽግና ማሳያ መኾኑንም ነው የገለጹት። የተጀመረውን ልማት የበለጠ ለማሳደግ እና ሕዝቡን እና ከተማዋን የሚገባቸው ከፍታ ላይ ለማድረስ ብልጽግና እንደሚሠራም ለኅብረተሰቡ ቃል ገብተዋል።
እንደ ሀገር የገባነውን ቃል በተገባር ፈጽመን እና የጀመርነውን ለማጠናቀቅ ብሎም ተጨማሪ ለመሥራት አቅደን ከፊታችሁ ቆመናል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል መንገድ ትራንስፖርትና ሎጅስቲክ ቢሮ ኀላፊ እና የጉባላፍቶ ምርጫ ክልል የክልል ምክር ቤት እጩ ተወዳዳሪ ጋሻው አወቀ (ዶ.ር) ብልጽግና ፓርቲ ባለፉት አምስት ዓመታት የሠራቸው ተግባራት የሚያኮሩ እንደኾኑ ገልጸዋል።
የወልድያ ከተማ ሕዝብም በችግር የማይበገር ጠንካራ ሕዝብ መኾኑን አሳይቷል ያሉት ኀላፊው፤ ነዋሪው የሚያሳየው ተሳትፎ እና ድጋፍ የብልጽግናን ጉዞ ያሳልጣል ነው ያሉት።
በመኾኑም ለሰላም፣ ለልማት እና ለተሻለ ነገ የወልድያ ከተማ ሕዝብ ከብልጽግና ጎን በመቆም እንዲሠራም ጠይቀዋል።
#7ኛው_ጠቅላላምርጫ #ወልድያ #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
