“ሕዝበ ሙስሊሙ የኢድ ዓል አደሃ በዓልን ሲያከብር የተቸገሩትን ወገኖች በማሰብና በመደጋገፍ ይሁን” የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት

9

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት 1ሺህ 447ኛውን የዒድ አል አደሃ (አረፋ) በዓል አከባበርን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኀን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

መግለጫውን የሰጡት የምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ አሕመድ ካሳ 1ሺህ 447ኛው የዒድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓል በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ ትልቅ ስፍራ ካላቸው በዓላት አንዱ ነው ብለዋል።

የሃይማኖቱ ተከታዮች በዓሉን ሲያከብሩ ሃይማኖታዊ አስተምህሮዎችን እና ማኅበራዊ እሴቶችን ባገናዘበ መልኩ ሊኾን እንደሚገባ አሳስበዋል።

“በዕለቱ አሏህ ዱዓችንን የሚሰማበት እና የሚቀበልበት በመኾኑ አማኞች ወደ ጋራ መስገጃ አደባባይ በመሄድ የዒድ ሶላትን በጋራ ሊሰግዱ ይገባልም” ብለዋል።

አረፋ የይቅርታ፣ የአብሮነት፣ የፍቅር እና የመተሳሰብ በዓል በመኾኑ አማኞች በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉ እና ችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን በመደገፍ እና በማሰብ በዓሉን ማክበር እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።

በክልላችን ብሎም በሀገራችን ዘላቂ እና አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን ሕዝበ ሙስሊሙ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።

ምክር ቤቱ ለመላው የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፈ ሲኾን በዓሉ የሰላም፣ የደስታ እና የፍቅር እንዲኾን መልካም ምኞቱን ገልጿል።

ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ

#አሚኮ_ዜና #የዒድ_አልአደሃ #አረፋ_በዓል #ባሕር_ዳር #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous article“ምርጫ ላይ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ በዴሞክራሲ ብቻ የሚያምን ትውልድ ለመፍጠር ያግዛል” መምህራን
Next articleየወልድያን ልማት ለማሳለጥ ምርጫውን በውጤታማነት መፈጸም ይገባል።