
ባሕር ዳር: ግንቦት 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 1 ሺህ 447ኛው የዒድ አል አደሃ (አረፋ) በዓል የእርስ በእርስ ጥላቻን በማራቅ፣ በይቅርታ እና በትህትና ለጋራ ሰላም የምንቆምበት ሊኾን ይገባል ሲል የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አሳስቧል።
የጉባኤው ሠብሣቢ ሼህ ማህመድ ኢብራሂም ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት በዓሉ ነቢዩ ኢብራሂም ለፈጣሪያቸው ያሳዩትን ፍጹም ታዛዥነት እና የከፈሉትን መስዋዕትነት የምናስብበት ታላቅ ዕለት ነው።
ይህ የነቢዩ ቁርጠኝነት ለሰው ልጆች ሁሉ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ያነሱት ሠብሣቢው “እኛም ለክልላችን እና ለሀገራችን ሰላም ስንል ከጥላቻ እና ከእርስ በእርስ ግጭት መራቅ አለብን” ብለዋል።
ሰላም የሚገኘው በይቅርታ፣ በትህትና እና ለሕዝብ ደኅንነት ሲባል ራስን ዝቅ በማድረግ በመኾኑ ልዩነቶችን በውይይት መፍታት ይገባልም ብለዋል።
በዓሉ የእርድ እና የመረዳዳት በመኾኑ የታመሙትን፣ የተፈናቀሉትን እና አቅም የሌላቸውን ወገኖች በመጠየቅ ብሎም ማዕድ በማጋራት በደስታ እንዲያሳልፉ ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ለዘመናት የዘለቀውን የሃይማኖቶች መከባበር እና መተሳሰብ ይበልጥ አጠናክሮ ለትውልድ ማስተላለፍ የሁሉም ኀላፊነት ሊኾን እንደሚገባም አሳስበዋል።
የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤው ለመላው የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፈ ሲኾን በዓሉ የሰላም፣ የፍቅር እና የይቅርታ እንዲኾን ምኞቱን ገልጿል።
1ሺህ 447ኛው የዒድ አል-አደሃ (አረፋ) በዓል ግንቦት 19/09/2018 ዓ.ም በእሥልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት እንደሚከበርም ተጠቁሟል።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
