“የትራንስፖርት ቁጥጥሩ ለተጓዦች እፎይታን እያመጣ ነው” ተገልጋዮች

8
ባሕር ዳር: ግንቦት 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የነዳጅ ቀውስ በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ ባሳደረው ተጽዕኖ ማኅበረሰቡን ለእንግልት ሲዳርግ ተስተውሏል። ይህንን ችግር ለመቅረፍም የተለያዩ የመፍትሔ አማራጮች ተግባራዊ እየተደረጉ ይገኛሉ።
በባሕር ዳር ከተማ ጎጃም በር መናኸሪያ በነዳጅ እጥረት ሰበብ የነበረው የሕዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች እጥረት እና ሕገ ወጥ የታሪፍ ጭማሪ በአሁኑ ሰዓት እየተቀረፈ መኾኑን ተገልጋዮች ነግረውናል ።
ተጓዦች ቀደም ሲል ከሦስት ቀን በላይ በመጉላላት ለአላስፈላጊ ተጨማሪ ወጭዎች ይዳረጉ እንደነበር ነው የገለጹት። አሁን ላይ በአንጻራዊነት መሻሻሉንም ተናግረዋል። ይህ አገልግሎት አሰጣጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ጠቁመዋል።
የአማራ ክልል መንገድ ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ቢሮ የትራንስፖርት ኢንስፔክሽን ዳይሬክተር አበባው ታደሰ የነዳጅ አቅርቦቱ በመሻሻሉ የጉዞ ስምሪት የሚያገኙ ተሽከርካሪዎች ቁጥር ጨምሯል ብለዋል።
በዚህም ከፍተኛ የትራንስፖርት ክፍተት የነበረባቸው መስመሮች በአሁኑ ወቅት በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ ነው ያሉት።
​የነዳጅ እጥረቱን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ከታሪፍ በላይ የሚያስከፍሉ እና ትርፍ የሚጭኑ ሕገ ወጥ አሽከርካሪዎችን ለመቆጣጠር ከተለያዩ አካላት ጋር በቅንጅት በመሥራት ሕጋዊ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል።
የተጀመረው የተቀናጀ የቁጥጥር ተግባር በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
​ኅብረተሰቡም በጉዞ ወቅት ያልተገባ ሕገ ወጥ አሠራር በተመለከተ ጊዜ ጥቆማ በመስጠት የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
Previous articleሀሰተኛ መረጃዎች በምርጫ ሂደት ምን ያስከትላሉ?