
በምዕራብ ጎጃም ዞን በሰከላ ወረዳ ለዚሁ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ በመከናወኑ ነዋሪዎች የምርጫ ካርዳቸውን በእጃቸው አድርገው የምርጫ ቀኑን በጉጉት እየተጠባበቁ እንደሚገኙ ከአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ጋር በነበራቸው ቆይታ ነግረውናል።
በወረዳው የሚንቀሳቀሱ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ዕጩዎቻቸውን እና ማኒፌስቶዎቻቸውን ለኅብረተሰቡ የማስተዋወቅ እና የማስገንዘብ ሥራ እየሠሩ መኾኑን ነዋሪዎቹ ይናገራሉ። ከዚሁ ከተሰጣቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በመነሳትም “ይበጀኛል” የሚሉትን ፓርቲ መርጠው ድምጽ ለመስጠት ሙሉ ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ማኅበረሰቡ ራሱ በመደራጀት የሰላም ማስከበር ሥራዎችን በባለቤትነት እየሠራ እንደሚገኝም አውስተዋል። ምርጫው ፍትሐዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ሰላማዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ የሰላም ባለቤት በመኾን የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡም ነው የተናገሩት።
ዕውነተኛ ሰላም፣ ልማት እና ምርታማነት ሊረጋገጥ የሚችለው ሕዝቡ “ይኾነኛል” ለሚለው በነፃነት ድምጹን ሰጥቶ ሲመርጥ ብቻ መኾኑን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል። በምርጫው ዕለት በነቂስ በመውጣት የዜግነት ግዴታቸውን እና የራሳቸውን የታሪክ አሻራ ለማስቀመጥ ቀኑን በደስታ እየተጠባበቁ መኾናቸውንም ነው ያስረዱት።
ዘጋቢ፦ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
