
ባሕር ዳር: ግንቦት 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በታሪኳ ስድስት ሀገራዊ ምርጫዎችን ከዚህ በፊት አካሂዳለች። እነዚህ የምርጫ ሂደቶች በሀገሪቱ የፖለቲካ ጉዞ ውስጥ ታሪክ፣ ተስፋ እና ትምህርት ጥለው አልፈዋል።
የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁሩ ሀሳቡ ተስፋ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ የተደረጉ ምርጫዎች የታሪክ ሂደት የፖለቲካ ምህዳሩን በመቅረጽ፣ የመንግሥታትን የሥልጣን መሠረት በማጽናት እና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን በማለማመድ ረገድ ሀገራዊ ተጽዕኖ እንደነበራቸው ተናግረዋል።
ሕዝብ በምርጫ የሚፈልገውን መንግሥት እያመጣ እና ውክልና እየሠጠ የሚሄድበት የፖለቲካ ባሕል ያስፈልጋል ያሉት ምሁሩ ሥልጣንን በኀይል ማሰብ የሕዝብ ህልውና፣ የሀገር ሉዓላዊነት እና አንድነት ሊረጋገጥ እንደማይችል ተናግረዋል።
በኀይል ከሚደረግ የሥልጣን ፍላጎት መውጣት ያስፈልጋልም ብለዋል። ምርጫ ወደ ዴሞክራሲ ልምምድ መውሰጃ እንደኾነ ነው የጠቆሙት። ለዚህም ምርጫ ማካሄድ ግድ እንደሚል ነው የተናገሩት።
ቀደም ሲል በኢትዮጵያ የተካሄዱ ምርጫዎች ዴሞክራሲን በማለማመድ የራሳቸው አበርክቶ እንደነበራቸው አንስተዋል።
ፖለቲካዊ መፍትሔ የሚሠጥባቸው ጉዳዮች ላይ መፍትሔ ለመስጠት የተመረጠ፣ ሀገሪቱን ሊያሥተዳድር የሚችል፣ ሕግ እና ሥርዓት ሊያሰፍን የሚችል ሥልጣን ያለው አካል ያስፈልጋል ብለዋል።
በሚያጎለውም ሊጠየቅ የሚችል እና ይህን አድርግ ይህን አታድርግ ሊባል የሚችል አካል መኖር አለበት ሲሉም በአጽንኦት አስረድተዋል። ለዚህ ደግሞ ምርጫ ማካሄድ ግድ እንደሚል ነው ያስገነዘቡት።
“የሕዝብ ይኹንታ ያለው አካል የሚመጣው በምርጫ ነው” ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
