
ባሕር ዳር: ግንቦት 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የወረዳው ነዋሪዎች ለአሚኮ እንደተናገሩት ምርጫው የሀገር እና የሕዝብን ቀጣይ እጣ ፋንታ የሚወስን መኾኑን በመገንዘብ በንቃት ለመሳተፍ ተዘጋጅተዋል።
ሀሳባቸውን ለአሚኮ የሰጡ የወረዳው ነዋሪ እንደተናገሩት በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በመሳተፍ የዜግነት ኀላፊነታቸውን ለመወጣት ቀደም ብለው የምርጫ ካርድ አውጥተዋል። 
ነዋሪው እንደሚሉት ምርጫው ለቀጣይ ሰላም እና ልማት ቁልፍ ሚና እንዳለው በጽኑ በማመን ዛሬ ላይ የተገኘውን ዕድል በመጠቀም ተወካያቸውን ለመምረጥ ተዘጋጅተዋል። 
ሌላኛው የወረዳው ነዋሪ እንደተናገሩት በፊት ባጋጠመው የጸጥታ መደፍረስ ምክንያት ስጋቶች እንደነበሩ ጠቁመዋል።
የታች ጋይንት ወረዳ ተወካይ ዋና አሥተዳዳሪ ሙሉጌታ አምሳሉ እንደተናገሩት ባለፉት ጊዜያት በወረዳው የጸጥታ መደፍረስ ተከስቶ ቆይቷል።
ነገር ግን በሕዝቡ፣ በክልሉ የጸጥታ ኀይል እና በሀገር መከላከያ ሠራዊት ቅንጅት አካባቢውን ወደ ሰላም በመመለስ ለምርጫው አስፈላጊው ዝግጅቶች መደረጋቸውን ተናግረዋል።
ምርጫው ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ያለውን ፋይዳ በመገንዘብ ኅብረተሰቡ በንቃት እንዲሳተፍ ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠር ሥራዎች ሢሠሩ መቆየታቸውን ጠቁመዋል። 
ለምርጫው ስኬታማነትም ሕዝቡ እስከ መጨረሻው ድረስ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል አቶ ሙሉጌታ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
