
ፍኖተሰላም: ግንቦት 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎጃም ዞን በደምበጫ ከተማ ከ53 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተገነቡ የተለያዩ የልማት ሥራዎች ተጠናቅቀው የክልል እና የዞን መሪዎች በተገኙበት ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ኾነዋል።
የትምህርት ቤት እድሳት እና አዲስ ግንባታ፣ 700 ሜትር ርዝመት ያለው የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ ሥራ፣ የማኅበረሰብ መድኃኒት ቤት፣ ድልድይ ግንባታ እና ሌሎች የልማት ሥራዎች ናቸው የተመረቁት።
የደምበጫ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ሙሉቀን መኮነን ከሰላም ግንባታ ጎን ለጎን ኅብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ አየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል። ተመርቀው ለአገልግሎት የበቁ የልማት ሥራዎች ለበርካታ ዓመታት የኅብረተሰቡ ጥያቄ ኾነው የቆዩ ናቸው ብለዋል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ዕድሜዓለም አንተነህ መንግሥት ኅብረተሰቡን በማሳተፍ በተጨባጭ ሠረቶ እያሳየ ነው ብለዋል።
ኅብረተሰቡን በማስተባበር ችግሮችንም ለመፍታት እንደሚተጉ አንስተዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ ድረስ ሳኅሉ (ዶ.ር) የክልሉ መንግሥት በአንድ በኩል ሰላምን በማረጋጋት በሌላ በኩል ደግሞ ሕዝቡን የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ ነው ብለዋል።
ልማትን በራሱ የሰላም ማጽኛ ዘዴ አድርጎ በመውሰድ የተሻሉ የልማት ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል።
አስተያየታቸውን የሰጡ የከተማው ነዋሪዎች በበኩላቸው በልማት ሥራዎች ላይ እያደረጉት ያለውን ተሳትፎ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
