የንጹሕ ውኃ አቅርቦትን እና የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ያረጋገጠው የማንጎ ልማት።

5
ባሕር ዳር :ግንቦት 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በሰሜን ወሎ ዞን ላስታ ወረዳ የማንጎ ኩታገጠም ልማትን ጎብኝተዋል።
የሥራ ኀላፊዎቹ በሹምሽሃ 023 ቀበሌ በመገኘት በፀሐይ ብርሃን (ሶላር ሲስተም) የሚሠራን የንጹሕ የውኃ መጠጥ አቅርቦትን ተመልክተዋል።
የቋሚ ተክል ሲንከባከቡ ያገኘናቸው አርሶ አደር ሲሳይ አበባው አካባቢው ለልማት ሲፈለግ ካሳ ተቀብለው መልቀቃቸውን ነግረውናል።
ከካሳ ክፍያ በተጨማሪ በቋሚነት ተቀጥረው 7ሺህ ብር እየተከፈላቸው እየሠሩ መኾኑን ጠቁመዋል። ሕዝብ ተጠቃሚ በመኾኑ ደስተኛ መኾናቸውንም ገልጸዋል።
የላሊበላ ውኃ እና ፍሳሽ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ መለሰ አየለ አራት ጥልቅ የውኃ ጉድጓዶች ለላሊበላ ከተማ ነዋሪዎች የንጹሕ ውኃ መጠጥ እያቀረቡ መኾኑን ተናግረዋል።
ጥልቅ ጉድጓዶቹ በክልሉ መንግሥት በጀት የተሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል። ለውኃ ልማት ሥራ የተነሱ 35 አርሶ አደሮች በቦታው የቋሚ ተክል እንዲያለሙ እና እንዲንከባከቡ መሠራቱን አንስተዋል።
የሰሜን ወሎ ዞን አሥተዳዳሪ አራጌ ይመር የሹምሽሃ ቀበሌን ተሞክሮ ለማስፋት እየተሠራ ነው ብለዋል። የላሊበላን ከተማ የንጹሕ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ተደራሽ ለማድረግ መሠራቱንም አንስተዋል።
የጥልቅ ጉድጓዶቹ የውኃ ፍሰታቸው ሲቀንስ ለመጨመር የመስኖ ልማት፣ አትክልት እና ፍራፍሬ በቦታው እንዲለማ መደረጉን ገልጸዋል።
ይህም በመኾኑ የውኃ ፍሰቱን መጨመር ተችሏል ነው ያሉት። ዝርያቸው የተሻሻለ የማንጎ ዝርያዎችን መጠቀማቸውንም ገልጸዋል። የአርሶ አደሮች ተጠቃሚነት መረጋገጡንም አንስተዋል።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) የላሊበላን ከተማ የውኃ አቅርቦትን ለማሻሻል እና የጥልቅ ጉድጓዶችን የውኃ ፍሰት ለመጨመር የቋሚ ተክል ልማቱ እገዛ ማድረጉን ተናግረዋል።
ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ያላቸው ተክሎች መልማታቸውንም አንስተዋል። የአካባቢው መልማት የአረንጓዴ ልማትን የሚያሳድግ እና አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
ከሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያ ይልቅ የተፈጥሮ ማዳበሪያን ተጠቅሞ በማልማት የንጹሕ መጠጥ ውኃን ከብክለት መታደግ እንደተቻለ አንስተዋል።
ለአርሶ አደሮች ካሳ ተከፍሏቸው ቢነሱም በቦታው ተቀጥረው ማንጎን በመንከባከብ ደመወዝ እየተከፈላቸው ዘላቂ ገቢ እንዲያገኙ ተደርጓል ነው ያሉት።
የአካባቢውን የአረንጓዴ ልማት ለመመለስ እየተሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል። የማይለሙ አካባቢዎች እንዲለሙ ተሞክሮ የተገኘበት መኾኑንም አንስተዋል።
የማይለሙ አካባቢዎችን በማልማት አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ ይሠራልም ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
Previous articleብልጽግና ፓርቲ ለወጣቶች ተጠቃሚነት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው።
Next articleምርጫ የሥልጡንነት መገለጫ!