
ገንዳ ውኃ፡ ግንቦት 05/2018ዓ.ም (አሚኮ) የምዕራብ ጎንደር ዞን አሥተዳደር 30ኛውን የሚሊሻ ምሥረታ በዓል አክብሯል። በመድረኩ ላይ ከፍተኛ የክልልና የዞን የሥራ ኀላፊዎች፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ጄኔራሎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ሚሊሻው የሀገርን ዳር ድንበር እና የሕዝብን ሰላም ሲያስከብር የቆየ መኾኑን የሚሊሻ አባላቱ ተናግረው በቀጣይም አካባቢውን ሰላም በማድረግ የሕዝቡን ደኅንነት ለመጠበቅ እንደሚሠሩ አጋግጠዋል።
የሕግ የበላይነትን ለማስከበር እና የማኅበረሰቡን ደኅንነት ለመጠበቅ ቁርጠኛ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
የበዓሉ ዓላማ ለሀገር ሰላም እና ለሕዝባቸው ደኅንነት የሚሠሩትን ለመዘከር እና ለማበረታታት ያለመ ነው ያሉት የምዕራብ ጎንደር ዞን ሚሊሻ መምሪያ ኀላፊ ባይመሽ ሰንደቄ ናቸው።
የሚሊሻ አባላቱን ተገቢውን ሥልጠና በመስጠት እና በአቅም በማዘጋጀት የአካባቢውን ብሎም የክልሉን ሰላም ለማስከበር ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል።
አባላቱን በሥነ ልቦና በማጠንከር እና በአደረጃጀት አቅማቸውን በማሳደግ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር እንሠራለን ነው ያሉት።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ እያሱ ይላቅ እንደተናገሩት የሚሊሻ አባላቱ ከሌሎች የጸጥታ መዋቅር ጋር በመቀናጀት ለሀገር ሰላም እና ለሕዝብ ደኅንነት ደጀን በመኾን ሌት ተቀን እየሠራ ያለ ኀይል ነው ብለዋል።
የሚሊሻ አባላት ባለፉት ሦሥት አሥርት ዓመታት የሕዝብን ሰላም በማስከበር እና በልማት ሥራዎች ላይ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መኾኑንም ተናግረዋል።
በቀጣይ አባላቱን በማጠናከር የአካባቢውን ሰላም በማስፈን የምርጫ ሥራዎችን በተገቢው መንገድ እንዲከናወኑ ይሠራል ብለዋል።
የአማራ ክልል የርእሰ መሥተዳድሩ የአሥተዳደር ጉዳዮች አማካሪ ጥላሁን መኳንንት የሚሊሻ አባላቱ ለአካባቢው እና ለክልሉ ሰላም መረጋጋት ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል ነው ያሉት።
ሰላም በነፃ የሚገኝ ሳይኾን በሚሊሻ አባላቱ እና በሌሎች የጸጥታ አካላት ደም፣ አጥንት እና ተጋድሎ የሚገነባ ውድ ሀብት መኾኑንም ገልጸዋል።
የክልሉ መንግሥት አባላቱን ለመደገፍ እና ለማበረታታት ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
ቀጣናውን ሰላም በማድረግ ከማኅበረሰቡ ጋር በመቀናጀት የምርጫን ሥራ በሰላም እንዲጠናቀቅ ሥራዎች መሠራት እንዳለባቸው አቶ ጥላሁን አሳስበዋል።
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
