
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 04/2018ዓ.ም (አሚኮ) የምርጫ ሂደት ሰላማዊ፣ ነፃ እና ፍትሐዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ የፖሊስ ሚና ወሳኝ ነው። የሕዝብን ደህንነት በመጠበቅ ማኅበረሰቡ ነጻ ኹኖ በምርጫ እንዲሳተፍም ትልቅ አደራም አለበት።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነርና የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር አበበ ውቤ የክልሉ ፖሊስ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ ከክልል እስከ ቀበሌዎች ድረስ በቂ ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን ተናግረዋል። ለውጤታማነቱም ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር ከእቅድ ጀምሮ በቅንጅት እየሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ለፖሊስ አባላት የግንዛቤ ፈጠራ መድረክ ፈጥሯል፣ የምርጫ ቁሳቁሶች ሰላማዊ በኾነ ኹኔታ እንዲንቀሳቀሱ እየተደረገም ነው ብለዋል። በምርጫ ቀንም ሕዝቡ የመሠለውን የፖለቲካ ፓርቲ ያለ ስጋት በነጻነት ወጥቶ እንዲመርጥ የተጠናከረ የወንጀል መከላከል ሥራ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
ፖሊስ በሕግ የሚፈቀድለትን የሙያ መመሪያ እና ሥርዓት መሠረት አድርጎ ከሕዝቡ እና ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር ይሠራል ብለዋል። ለዚህም ሕዝቡ የምርጫው ባለቤት ኹኖ ለጸጥታ ሥራ አጋር እንዲኾን ጠይቀዋል። ሕዝቡ የምርጫው ባለቤት ሊኾን እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
እስካሁን ካለው የምርጫ ሂደት ጋር ተያይዞ በተሠራ የጸጥታ ሥራ ያጋጠመ ችግር አለመኖሩንም ጠቅሰዋል።
ሀገራዊ ምርጫው ሰላማዊ እና ዲሞክራሲያዊ ኹኖ እንዲጠናቀቅ ፖሊስ በታማኝነት እና በቁርጠኝነት እንደሚሠራም ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
