ለሰላማዊ ምርጫ ሴቶች ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል።

13
ባሕር ዳር: ግንቦት 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነጻ፣ ፍትሐዊ እና ተአማኝነት ያለው ኾኖ እንዲጠናቀቅ ሴቶች በግንባር ቀደምትነት ሊሳተፉ ይገባል።
ወይዘሮ ምንታምር ዘለቀ የቻግኒ ከተማ ነዋሪ ናቸው። በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ይበጀኛል የሚለውን ፓርቲ ለመምረጥ ዝግጅት ላይ መኾናቸውን ነግረውናል።
ባለፉት ስድስት የምርጫ ጊዜያት የሚፈልጉትን ፓርቲ ሲመርጡ እንደቆዩም አስታውሰዋል። ዘንደሮም ለሰባተኛ ጊዜ እንደሚመርጡ ነው የተናገሩት።
ሴቶች ከመምረጥ ባለፈ የሰላም አምባሳደር መኾን እንዳለባቸውም ገልጸዋል። ምርጫ ላይ የሴቶች ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱንም ተናግረዋል።
ምርጫው ሰላማዊ እና ፍትሐዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ ሴቶች የእናትነት፣ የእህትነት እና የሰላም አምባሳደር ኾነው ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አንስተዋል።
ሴቶች ቤተሰብን፣ ጎረቤትን እና የአካባቢው ማኅበረሰብን የመምከር እና የመመለስ ድርሻችን ከፍተኛ በመኾኑም በትኩረት መሥራት ይኖርብናል ብለዋል።
ሴቶች ይወክለኛል የሚሉትን ፓርቲ በያዙት የምርጫ ካርድ መምረጥ እንዳለባቸው የተናገሩት ደግሞ ሌላኛዋ ከአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ጋር ቆይታ ያደረጉት የግምጃ ቤት ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ አልጋነሽ አስፋው ናቸው።
ለሦስተኛ ጊዜ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ እየተጠባበቁ መኾናቸውን ነግረውናል። የዘንድሮው ምርጫ ለኔ ታሪካዊ ነው ብለዋል። ምክንያቱም የመጀመሪያ ልጄ ለመጀመሪያ ጊዜ ምርጫ ይመርጣል ነው ያሉት።
የምርጫ ካርድ ቀድመው ከባለቤታቸው እና ከልጃቸው ጋር በእጃቸው ማድረጋቸውንም አንስተዋል። ማንኛውም ሰው የሚፈልገውን ፓርቲ በሰላማዊ መንገድ መምረጥ እንዳለበትም መክረዋል።
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

See less
Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) ዋና ዳይሬክተር ክርስታሊና ጆርጂየቫ ጋር ተወያዩ።
Next articleበትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሠረተ ምርጫ የዴሞክራሲ መሠረት ነው።