
ባሕር ዳር: ግንቦት 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በሌማት ቱርፋት መርሐ ግብር በትኩረት እየተሠራባቸው ከሚገኙ ዘርፎች መካከል የዓሣ ሀብት ልማት አንዱ ነው።
ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግም የአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ቢሮ ለዓሣ አስጋሪ ማኅበራት እና ባለሙያዎች በዓሣ ማስገሪያ መረብ ዙሪያ ሥልጠና ሰጥቷል።
የአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ቢሮ የእንስሣት እርባታ፣ ተዋጽኦ እና መኖ ልማት ዳይሬክተር መኳንንት ዳምጤ የዓሣ ሀብትን ለማልማት ከሚያስፈልጉ ግብዓቶች መካከል የዓሣ ማስገሪያ መረብ አቅርቦት አንዱ ነው ብለዋል።
እስከ አሁን ድረስ በአብዛኛው ጥቅም ላይ ሲውሉ የቆዩት የዓሣ ማስገሪያዎች በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ መኾናቸውን ተናግረዋል። ይህ ተገቢ ያልኾነ ማስገሪያም ትናንሽ ዓሳዎችን ጭምር የሚይዝ እና የዓሣ ዝርያው እንዲመናመን የሚያደርግ መኾኑን አስረድተዋል።
ይህንን ግምት ውስጥ በማስገባት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ደረጃውን የጠበቀ የዓሣ ማሥገሪያ መረብ 115 ለሚኾኑ የማኅበራት ተወካዮች እና ባለሙያዎች የተግባር ሥልጠና መሰጠቱን አብራርተዋል።
በቀጣይም ሥልጠናውን በማስፋት ደረጃውን የጠበቀ የዓሣ ማስገሪያ መረብ በስፋት ለማቅረብ ከናቡ ኢትዮጵያ ጋር ስምምነት ተወስዶ እየተሠራ መኾኑን አመላክተዋል።
የሥልጠናው ተሳታፊ ወይዘሮ እናንየ ታምሩ ባገኙት ሥልጠና መሰረት ትላልቅ አሳዎችን ብቻ የሚይዙ እና ትናንሾቹ እንዲያድጉ ዕድል የሚሰጡ መረቦችን ማዘጋጀት መቻላቸውን ተናግረዋል። ሥልጠና ማግኘታቸውም እንዳስደሰታቸው እና ለውጤታማነት እንደሚያነሳሳቸው ገልጸዋል።
ሌላኛው የሥልጠናው ተሳታፊ እና የምዕራብ ጎጃም ዞን እንስሳት እና ዓሣ ሀብት ልማት መምሪያ የዓሣ ሀብት ልማት ባለሙያ ሻሬ አቤ ሥልጠናው በዘርፉ ውጤታማ የዓሣ ምርት ለማግኘት አቅም የሚፈጥር መኾኑን አንስተዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
#አሚኮ #አማራ ኢትዮጵያ #ሌማት_ቱርፋት #ዓሣ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
