
ባሕር ዳር፡ ሚያዚያ 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በተለዋዋጭ ዓለም ውስጥ ትውልድን የማነጽ ጉዞ በበርካታ ተግዳሮቶች የታጠረ ነው።
ከመማሪያ መጽሐፍት ይዘት እስከ ተማሪዎች የመቀበል አቅም ልዩነት ድረስ ያሉት መሰናክሎች የትምህርት ጥራትን በየዕለቱ ይፈታተኑታል።
ታዲያ ይህንን ክፍተት ለመሙላት እና የትምህርት ዘርፉን በሳይንሳዊ ዕውቀት ለማገዝ፣ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ 13ኛ ዙር የጥናት እና ምርምር ሲንፖዚየም አካሂዷል። መድረኩም መምህራን ከክፍል ውስጥ ተግዳሮት ወደ መፍትሔ አመንጭነት የተሸጋገሩባቸውን ሥራዎች የተመለከተ ነበር።
በአንድ ጠባብ ክፍል ውስጥ ከ50 በላይ ተማሪዎችን እየተከታተሉ ማስተማር ለብዙዎች መምህራን ፈተና ነው። የእነዚህ ተማሪዎች የመሠረታዊ ሒሳብ ስሌት አቅም ዝቅተኛ መኾን ደግሞ ፈተናውን ይበልጥ ያከብደዋል።
መምህር ረዳ ተዘራ በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የመስከረም 16 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የሂሳብ መምህር ናቸው።
በአንድ ክፍል ከሚያስተምሯቸው 56 ተማሪዎች መካከል ሰባቱ ተማሪዎች በሒሳብ መሠረታዊ ስሌት ላይ የነቃ የተሳትፎ ችግር እንደነበረባቸው አንስተዋል።
ይህ ችግር ተግባራዊ ጥናት እና ምርምር ለማድረግ እንዳነሳሳቸው አንስተዋል። የሒሳብ ስሌት የሚከብዳቸውን ሰባት ተማሪዎች ለይተው ባደረጉት ተግባራዊ ምርምር የአጠናን እና የማስተማር ሥነ ዘዴውን ከሌሎች በተለየ በመከታተል የስድስቱን ተማሪዎች አቅም መቀየር ችለዋል።
ይህ የሳቸው ስኬት በባሕር ዳር ከተማ ለ13ኛ ዙር በተካሄደው የጥናት እና ምርምር ሲንፖዚየም ላይ ከቀረቡ በርካታ የጥናት ውጤቶች መካከል አንዱ ነው።
በሲንፖዚየሙ የጥናት ውጤታቸውን ያቀረቡት ሌላኛዋ የሰላም አካዳሚ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህርት ትበይን ስሜነህ ናቸው።
ተማሪዎቻቸው ፊደላትን መቅረጽ ተስኗቸው ነበር። ይህንን ተግዳሮት በዝምታ አላለፉትም። መፍትሔው ያለው በመማሪያ መጽሐፉ ውስጥ ብቻ ሳይኾን በአቀራረብ ዘዴ ላይ መኾኑን ተረዱ። መምህርት ትበይን በምርምር ባገኙት አዲስ የማስተማር ስልት የልጆቹን የጽሕፈት ችሎታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ማሳደግ ችለዋል።
በሲንፖዚየሙ ላይ የተገኙት የከተማ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ሙሉዓለም አቤ (ዶ.ር) እንደገለጹት፣ መምህራን በክፍል ውስጥ የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች በተግባራዊ እና መሠረታዊ ጥናት እና ምርምር መፍታት አለባቸው ብለዋል። ምርምር የተማሪዎችን ዕውቀት ብቻ ሳይኾን አመለካከት እና ክህሎትንም ጭምር የሚቀይር መኾኑን አንስተዋል።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
See less
