የፖለቲካ ፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳ ሲያደርጉ ሕጎችን ማክበር ይጠበቅባቸዋል።

8
ባሕር ዳር፡ ሚያዚያ 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሰባተኛው ጠቅላላ መርጫ ግንቦት 24/2018 ዓ.ም ሊካሄድ ቀን ተቆርጦለታል። የፖለቲካ ፖርቲዎች የራሳቸውን ማኒፌስቶ፣ መርሐግብር እና እቅዶቻቸውን እያስተዋወቁ ይገኛሉ።
የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ማድረግ የሚገባቸውን እና ማድረግ የሌለባቸውን ጉዳዮችን በተመለከተ በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የሕግ አገልግሎት ክፍል ዳይሬክተር አብዬ ካሳሁን ጋር ቆይታ አድርገናል። የፖለቲካ ፓርቲዎች ስለሚከተሏቸው ጉዳዮች የኢትዮጵያ ምርጫ፤ የፖለቲካ ምዝገባ እና ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 ላይ የተደነገጉ በርካታ ጉዳዮች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
በተለይ ፓርቲዎች በምርጫ ወቅት በሚያደርጉት ቅስቀሳ አንዱን ፓርቲ ሌላኛው ተፎካካሪ ፓርቲ እና ሕጎችን ማክበር ይገባዋል ብለዋል። አዋጁን ተከትሎ አለመሥራት ወደ ግጭት እና ብጥብት ሊያስገባ ይችላልም ነው ያሉት።
ፓርቲዎች በሰላማዊ መንገድ መቀስቀስ ይገባቸዋል ያሉት ዳይሬክተሩ በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ብሔርን ከብሔር ጋር እና ሃይማኖትን ከሃይማኖት ጋር የሚያጋጩ ንግግሮችን ማድረግ የለባቸውም ብለዋል።
ቅስቀሳ ለማድረግ በምርጫ ቦርድ ከተፈቀደ ጊዜ ጀምሮ ፓርቲዎች በተለያዩ ቦታዎች የራሳቸውን ዓላማ፣ ፖሊሲ እና መርሐግብር እያስተዋወቁ እንደኾነ ገልጸዋል። ነገር ግን ፓርቲዎች መቀስቀስ የማይገባቸው ቦታዎች እንዳሉ ተናግረዋል።
ከእነዚህሞ ውስጥ፡-
👉 በሃይማኖት ተቋማት
👉 በትምህርት ቤቶች
👉 በማረሚያ ቤቶች
👉 ሕዝብ በሚገበያይባቸው (የገበያ ቦታዎች)
👉 በፖሊስ ተቋማት እና
👉 በወታደራዊ ካምፖች ላይ የምረጡን ቅስቀሳ ማካሄድ የማይገባቸው ቦታዎች እና የሕግ ተጠያቂነትን የሚያስከትሉ መኾናቸውን ገልጸዋል።
ለፖለቲካ ፓርቲዎች ሰላማዊ እንቅስቃሴ ሁሉም ኀላፊነት እንዳለበት ተናግረዋል። የሲቪክ ማኅበራት፣ ሚዲያዎች እና ሌሎች በጎ ፈቃደኞችም ምርጫው ሰላማዊ ኾኖ እንዲካሄድ ኀላፊነታቸውን መወጣት ይገባቸዋል ብለዋል።
ማኅበረሰቡ ዴሞክራሲያዊ መብቱን በአግባቡ እንዲጠቀም በቂ ግንዛቤ መያዝ ያስፈልጋል ነው ያሉት። አሚኮን ጨምሮ ሌሎች ሚዲያዎች ነፃ የአየር ሰዓት ሰጥተው ፓርቲዎች ክርክር እንዲያደርጉ ማድረጋቸው ወሳኝ እንደኾነ ገልጸዋል።
በዓለም ያለ መንግሥት የሚተዳደር ሀገር እንደሌለ ያነሱት ዳይሬክተሩ ሕዝቡ ይኾነኛል፣ ይጠቅመኛል እና ይለውጠኛል የሚለውን ፓርቲ ለይቶ መምረጥ እንዲችል ኹሉም አካል መረባረብ እንዳለበት መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፦ሰለሞን ሰንታየሁ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

See less
Previous articleሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ዜጎችን ለውስብስብ ችግር እየዳረገ ነው።
Next articleየባሕር ዳር መምህራን የምርምር ስኬት!