የነዳጅ ዋስትና ጊዜው አብቅቷል።

4
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) “ኢራን ኒውክለር መታጠቅ የለባትም” በሚል የተጀመረው የኢራን እና የአሜሪካ ጦርነት የዓለምን መልክ ቀይሯል።
እንደ ሲኤንኤን ዘገባ የሆርሙዝ ሰርጥ ዘወትራዊ ዝውውር መስተጓጎል ዓለምን ወደ ንጹህ ኢነርጂ እንዲያዘነብል አድርጎታል። ታዳሽ ኀይል የመጠቀምን አስፈላጊነትም በጉልህ እያሳየ ቀጥሏል።
በዚህ ሂደት ቻይና 🇨🇳 ዓለም ትልቅ ተሞክሮ የወሰደባት ሀገር ኾናለች። እንዴት?
⚡️ ቻይና ሀገራዊ ደኀንነቷን እና ኢኮኖሚዋን ለማስጠበቅ በታዳሽ ኀይል ዘርፍ ቀድማ በነደፈችው ጥንቁቅ ስትራቴጅ አሁን በዘርፉ የዓለም መሪ መኾን ችላለች።
⚡️ አሁን ላይ ቻይና በዓለማችን ትልቋ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ፣ የንፋስ ተርባይን እና የሶላር ፓኔል አምራች ናት።
⚡️አሁን ብዙ ሀገራት በተለይም የእስያ እና የአፍሪካ ሀገራት ፊታቸውን ወደ ቻይና እያዞሩ እና ከፍተኛ የታዳሽ ኀይል ምርቶችን ከቻይና እየገዙ ነው።
🎯 ከጦርነቱ ወዲህ የቻይና የታዳሽ ኃይል ገበያ
🌤 ኤምብር የተሰኘው የኢነርጅ ጥናት ተቋም ባወጣው መረጃ መሠረት በቻይና የሚመረቱ የሶላር ቴክኖሎጂዎች፣ ባትሪዎች እና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የወጭ ንግድ በመጋቢት ወር በ 70 በመቶ ጨምሯል።
🌤 ሀገሪቱ በመጋቢት ወር ብቻ የባትሪ የወጭ ንግዷ 10 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል።
🌤 68 ጊጋ ዋት የሚያመነጭ የሶላር ቴክኖሎጅ ወደ ውጭ የላከች ሲኾን ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት አኳያ የ 50 በመቶ ብልጫ አለው።
🌤 ቻይና በታዳሽ ኀይል ቴክኖሎጂ ያላት የበላይነት ጂኦፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖዋን እንዲጨምር አድርጎታል።
👉እውን የኢራን-አሜሪካ ጦርነቱ የታዳሽ ኀይል ሽግግርን አፋጥኗል? የብሪታንያ የኢነርጂ መሥሪያ ቤት ጸሐፊ ኤድ ሚሊባንድ “ከአምስት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ የነዳጅ ቀውስ ማጋጠሙን በማንሳት የነዳጅ ዋስትና ጊዜው እንዳበቃ እና የንጹሕ ኢነርጅ ዋስትና ዘመን መምጣት እንዳለበት ትምህርት መውሰድ አለብን” ሲሉ ተደምጠዋል።
የኤምበር የኢነርጅ ጥናት ተቋም ከፍተኛ ተንታኝ ኢዩን ግርሃም በበኩላቸው “ሶላር ቀድሞውንም የዓለም ኢኮኖሚ ሞተር ኾኖ ነበር። አሁን ያለው የነዳጅ ዋጋ መናር ደግሞ የሶላር ሽግግሩን ይበልጥ ፈጣን አድርጎታል” በማለት ሀሳቡን አጠናክረውታል።
🇪🇹 ኢትዮጵያስ ?
ኢትዮጵያ የኀይል አቅርቦቷን ሙሉ በሙሉ ከታዳሽ የኀይል ምንጮች ለማግኘት ከነዳጅ ጥገኝነት ለመውጣት ብሎም በአፍሪካ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ መሪ ለመኾን መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ ውስጥ ትገኛለች።
ሀገራዊ ርዕዩን ለማሳካትም ከአነስተኛ የፀሐይ ኀይል ሥርጭት እስከ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ግንባታ ትኩረት ተሰጥቷቸዋል።
💫 ቀደም ብሎ ወደ ሥራ የገባው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ኀይል በማመንጨት ላይ ይገኛል። የኮይሻ የኀይል ማመንጫ ግድብም በግንባታ ላይ ነው።
💫 በቅርቡ የአሰላ የንፋስ ኀይል ማመንጫ ተመርቋል። በአዳማ እና በአሸጎዳ በሥራ ላይ የሚገኙትን ጨምሮ የአይሻ አንድ የንፋስ ኀይል ፕሮጀክት በግንባታ ላይ ነው።
በጥቅሉ መንግሥት በዘርፉ የጀመራቸው ጥረቶች ኢትዮጵያን የአፍሪካ የታዳሽ ኀይል ማዕከል እንደሚያደርጋት ታምኖበታል።
ዘጋቢ ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
Previous articleየቀድሞው የአማራ ክልል አፈ-ጉባኤ እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የነበሩት አምባሳደር ያለው አባተ ከዚህ ዓለም አረፉ።
Next articleለጥንቃቄ! የሰው ሠራሽ አስተውሎት አጠቃቀም