ቀድሞ እርሻ መጀመር ምርታማነትን ለማሳደግ ትልቅ ፋይዳ አለው።

11

 

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ግብርናውን በማዘመን በምግብ ራስን ከማስቻል ባለፈ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን ለማምረት ታልሞ እየተሠራ ይገኛል። የአማራ ክልልም የቅድመ ዝግጅት ተግባራት ተከናውነው የመኸር እርሻ እንቅስቃሴ መጀመሩን የክልሉ ግብርና ቢሮ ኀላፊ ደረጀ ማንደፍሮ ገልጸዋል።

በክልሉ ከ5 ነጥብ 58 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በመኸር እርሻ በተለያዩ ሰብሎች
ይሸፈናል። በ2018/19 የምርት ዘመንም ከ205 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሠብሠብ ታቅዶ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።

ምርታማነትን ለማሳካትም፦
👉 የኩታ ገጠም የእርሻ አሠራር ሥርዓት መዘርጋት
👉 የግብዓት፣ የአፈር ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር አቅርቦት

👉የአሲዳማ አፈርን የማከም ሥራ መሥራት ትኩረት የተደረገባቸው ናቸው።

በክልሉ 8 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግብዓት ለማቅረብ ታቅዶ እስካሁን 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበርያ እየተጓጓዘ ነው ብለዋል። ቀድመው ለሚዘሩ አካባቢዎች የአፈር ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር በማቅረብ ሥርጭት መደረጉንም ገልጸዋል።

የድጋፍ እና ክትትል ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት። አርሶ አደሮችም በወቅቱ ማሳቸውን በማለስለስ እና የግብዓት አቅርቦቱን በመጠቀም የእርሻ ማሳቸውን በዘር መሸፈን እንዳለባቸው አሳስበዋል።

መሬት ፆም ማደር እንደሌለበትም አስገንዝበዋል።
በሰሜን ጎጃም ዞን የደቡብ አቸፈር ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ለአሚኮ እንዳሉት የእርሻ ማሳቸውን እያለሠለሱ በዘር ለመሸፈን እያዘጋጁ ነው።

ቀድመው ለሚዘሩ ሰብሎች የሚኾን የአፈር ማዳበሪያ እና ዘር መግዣ ክፍያ ፈጽመውም እየተጠባበቁ እንደሚገኙ ተናግረዋል። አራት ሄክታር የእርሻ መሬት አለኝ የሚሉት አርሶ አደሩ
ባለፈው ዓመት የምርት ዘመን ቀድመው እርሻ በመጀመራቸው የተሻለ ምርት ማግኘታቸውን አስታውሰዋል።

ሌላኛው በምሥራቅ ጎጃም ዞን የባሶ ሊበን ወረዳ አርሶ አደር የእርሻ ማሳቸውን በትራክተር እያለሠለሱ መኾናቸውን ተናግረዋል። ቀድመው ለሚዘሩ ሰብሎችም ማዳበሪያ እና የበቆሎ ምርጥ ዘር ማግኘታቸውን የተናገሩት አርሶ አደሩ ባለፈው ዓመት ካገኙት ምርት የተሻለ ለማምረት እየተጉ መኾናቸውን ገልጸዋል።

ቀድሞ እርሻ መጀመር የሰብል ተባይን ለመቀነስ እና ምርታማነትን ለማሳደግ ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል።
ሌሎች አርሶ አደሮችም ቀድመው ማሳቸውን በማለስለስ በዘር መሸፈን እና ጠንክረው በመሥራት ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous articleቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የታዳሽ ኃይል ልማታችን የስበት ማዕከል ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
Next articleከይለፍ-ቃል ወደ ማለፊያ-ቁልፍ…