
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የልማት ሥራዎችምን ለመጎብኘት ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ገብተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ከሀገር ወዳዱ እና የምዕራቡ ጀግና ሼህ ሆጀሌ ምድር፣ አፈሩ ቢታረስ ልማት፣ ቢቆፈር ወርቅ ከሚታፈስበት እና በኅብር የመኖር ተምሳሌት ወደ ኾነው ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ገብተናል ብለዋል።
ክልሉ የኢትዮጵያ የልማት ሞተር እና የሕዝቦች የትብብር ተምሳሌት የኾነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድባችን መገኛ፣ የታዳሽ ኃይል ልማታችንም የስበት ማዕከል ነው።
በጥዑም የባሕላዊ የትንፋሽ መሳሪያቸሁ ዙምባራ የታጀበው ውብ መስተንግዷችሁ እና ደማቅ አቀባበላችሁም ልባችንን በሐሴት ሞልቶታል ነው ያሉት።
አሶሳ ሕዳሴ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ አቀባበል ላደረጉላቸው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርእሰ መሥተዳድር እና ካቢኔያቸው፣ ለክልሉ ከፍተኛ መሪዎች ፣ ለሃይማኖት አባቶች፣ ለሀገር ሽማግሌዎች እና ለአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ምስጋና አቅርበዋል።
በክልሉ በሚኖራቸው ቆይታ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን እንደሚጎበኙም ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
