ተማሪዎችን ማብቃት የነገ ሀገርን መገንባት ነው።

17
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ተማሪ ነጻነት ሀብታሙ በምሥራቅ ጎጃም ዞን ጎዛምን ወረዳ የገጠር ፋና አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የስምንተኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ተፈታኝ ናት።
በዕቅድ ጊዜዋን በአግባቡ በመጠቀም ለፈተና እየተጋች መኾኗን ተናግራለች። ከጓደኞቿ ጋር በመረዳዳት ጠንክራ እያነበበች ነው። መምህራን ከሚያደርጉት እገዛ በተጨማሪ ወላጆቿም ድጋፍ እያደረጉላት መኾናቸውን ገልጻለች።
በፈተናው የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ አቅዳለች። ሌሎች ተማሪዎችም ጊዜያቸውን በአግባቡ በመጠቀም ለፈተናው ከወዲሁ መዘጋጀት እንዳለባቸው ተናግራለች።
በምሥራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ የሥርዓተ ትምህርት ባለሙያ ወርቁ አባተ በዞኑ 108 ትምህርት ቤቶች ስድስተኛ እና 91 ትምህርት ቤቶች ደግሞ የስምንተኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና እንደሚያስፈትኑ ገልጸዋል።
7ሺህ 173 የ6ኛ እና 7ሺህ 860 የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች ፈተናውን ለመውሰድ በቴክኖሎጂ የታገዘ (ኦን ላይን) ምዝገባ ተከናውናል ብለዋል።
ተማሪዎችን ውጤታማ ለማድረግ በተመረጡ መምህራን እሁድ እና ቅዳሜን ጨምሮ የማካካሻ ትምህርት በትኩረት እየተሠጠ እንደኾነም ገልጸዋል። በሳምንቱ ሁሉንም ቀናት የቤተ መጻሕፍት አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል ነው ያሉት።
በጸጥታ ችግር ምክንያት መማር ያልቻሉ ተማሪዎችን ወደ ወረዳ ከተማ ማዕከላት በማምጣት የልዩ ድጋፍ ትምህርት መርሐ ግብር የመማር ዕድል እንዲያገኙ መደረጉንም ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ እየሩስ መንግሥቱ ሀገር እና ክልል አቀፍ ተፈታኝ ተማሪዎችን ለማብቃት አዳድስ ስልቶችን በመዘርጋት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
በትምህርት ቤቶች የመጻሕፍት ግብዓት ማሟላት እና የአዳር ጥናት እንዲኖር እየተደረገ ይገኛል ብለዋል። የትምህርት ይዘቱ በተያዘለት ዕቅድ እንዲያጠናቅቅ እየተደረገ መኾኑንም አንስተዋል። ተፈታኝ ተማሪዎች ብቁ እና ተወዳዳሪ ኾነው የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ጥረት እተደረገ መኾኑንም አስገንዝበዋል።
ከባለፈው ዓመት የተሻለ የተማሪ ቁጥር ክልል አቀፍ ፈተና እንደሚወስዱ ተናግረዋል። ለፈተናው በሥነ ልቦና ለማዘጋጀት ከዩኒቨርሲቲዎች እና ኮሌጅች ጋር በቅንጅት እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
ተማሪዎችን ማብቃት የነገ ሀገርን መገንባት በመኾኑ በተለይም ባለፉት ዓመታት የታዩ ጉድለቶችን በቁጭት ለማሻሻል በቅድመ ዝግጀት ምዕራፍ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ተፈታኝ ተማሪዎች የሚጠበቅባቸውን ዕውቀት ቀስመው የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ የትምህርት ባለ ድርሻ አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
Previous articleከ50 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የምርጫ ካርድ ወስደዋል።
Next articleሰው ተኮር የኾኑ የበጎ አድራጎት ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ።