
ባሕር ዳር፡ ሚያዚያ 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከሲዲሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዣን ካሴያ ጋር ተወያይተዋል። ይህንን አስመልክተው የሚከተለውን መልእክት አስተላልፈዋል፦
ዛሬ ጠዋት የአፍሪካ በሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (Africa CDC) ዋና ዳይሬክተር ከሆኑት ከዶክተር ዣን ካሴያ ጋር ውጤታማ ውይይት አድርገናል። በውይይታችን በተለያዩ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ላይ የመከርን ሲሆን፤ በተለይም በአፍሪካ ሕብረት የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) እና የዲጂታል ጤና ዘርፍ መሪ (Champion) በመሆን የተሰጠኝን አዲስ ኃላፊነት በሚመለከት በስፋት ተነጋግረናል።
የፈጠራ ሥራዎች ለአፍሪካ ዕድገት ምንጊዜም ወሳኝ መሰረት ናቸው። በጤናው ዘርፍ የሚገጥመንን ተለዋዋጭ ተግዳሮቶች ለመወጣት የሰው ሰራሽ አስተውሎትንና የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን ዐቅም መጠቀም የጤና ሥርዓታችንን ለማጠናከር፣ ተደራሽነትን ለማስፋፋት እና ለሕዝባችን የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ወሳኝ ነው።
ኢትዮጵያ ያላትን ልምድ ለአህጉሩ ለማካፈል እንዲሁም በፍጥነት ከሚለዋወጠው የቴክኖሎጂው ዓለም ጋር ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመራመድ የሚያስችሉ ጠንካራ አጋርነቶችን ለመመሥረት ያላትን ቁርጠኝነት ዳግም ታረጋግጣለች።
ይህንን ርዕይ ወደ ተጨባጭና አካታች ውጤት ለመለወጥ ከአፍሪካ ሲዲሲ (Africa CDC) እና በመላው አህጉሪቱ ከሚገኙ አጋሮች ጋር በቅርበት ለመሥራት ዝግጁ ነኝ።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
