
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥት አገልግሎት እና አሥተዳደር ሪፎርም ወደ ተግባር ከተገባ ሦስት ዓመታትን አስቆጥሯል።
በአማራ ክልልም ለሪፎርሙ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሲተገበሩ መቆየታቸውን የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኀላፊ ባንችአምላክ ገብረማርያም ገልጸዋል።
የመንግሥት ሠራተኞችን መረጃ የማጣራት፣ የማረጋገጥ እና በዲጂታል ሥርዓት መመዝገብ የሪፎርሙ አካል ነው ብለዋል። ይህም የዲጂታል ሲቪል ሰርቪስ ግንባታን የማረጋገጥ ሂደት መኾኑን ነው የተናገሩት።
ተግባሩን ለመጀመር ከክልል ጀምሮ በየደረጃው የሚያሥተባብር ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ተግባር እየተገባ መኾኑንም ገልጸዋል።
የመንግሥት ሠራተኞችም ለምዝገባው ፋይዳ የዲጂታል መታወቂያ መያዝ እና አስፈላጊውን መረጃ በማቅረብ መተባበር እንደሚገባ አሳስበዋል።
በየደረጃው ያሉ የተቋማት ኀላፊዎች እና ባለድርሻ አካላትም ትኩረት ሰጥተው የሚጠበቅባቸውን ኀላፊነት እንዲወጡ አስገንዝበዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት መምሪያ ኀላፊ ጤናው ምህረቱ የምዝገባ ሥርዓቱ ከወረቀት በመውጣት ትክክለኛ መረጃን በቴክኖሎጅ ለመያዝ እንደሚያስችል ተናግረዋል።
በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የሚያጋጥሙ የመረጃ መጥፋትን የሚታደግ አስተማማኝ ሥርዓት ስለመኾኑም ነው የገለጹት።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት መምሪያ ኀላፊ የሻረግ ታፈረ የመረጃ ምዝገባ ሥርዓቱ ለመንግሥት ሠራተኛው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።
የግል ማኅደር ለሠራተኛው የሕይወቱ አካል በመኾኑ በዲጂታል ሥርዓት መደራጀቱ ዋስትና የሚሰጥ ስለመኾኑ አንስተዋል። ለተግባራዊነቱም በቁርጠኝነት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
