
ደሴ: ሚያዝያ 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥት ሠራተኞችን መረጃ በማረጋገጥ ሥራ ላይ ለሚሠማሩ መረጃ ሠብሣቢዎች እና ተቆጣጣሪዎች ሥልጠና መስጠት ተጀምሯል።
ሥልጠናውን የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ከፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ጋር በመተባበር ነው የሚሰጡት።
በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ደሴ ቅርንጫፍም ወደ ሥራው ለሚሠማሩ 443 የቴክኒክ እና ሙያ መምህራን እና የስታቲስቲክስ ባለሙያዎችን በኮምቦልቻ ማሠልጠን ጀምሯል።
በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የደሴ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኡስማን መሐመድ ቆጠራው መካሄዱ የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞችን በየዘርፉ ለይቶ ዝርዝር መረጃ ለመያዝ የሚያግዝ ነው ብለዋል።
ከሕግ እና ሥርዓት ውጭ ተቀጥረው የሚገኙ ሠራተኞችን ለመለየት፣ “አንድ ሰው ለአንድ መደብ” የሚለውን መመሪያ ለመተግበር እና የመንግሥት ሠራተኞችን መለያ ቁጥር በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማዳረስ ያስችላል ነው ያሉት።
የጡረታ መለያ ቁጥር የሌላቸውን የመንግሥት ሠራተኞች በመለየት የጡረታ መለያ ቁጥር ባለቤት እንዲኾኑ በማድረግ የማኅበራዊ ዋስትና ተጠቃሚ ለማድረግም ያስችላል ብለዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞችን አሁናዊ መረጃ ተለይቶ መያዙ ለፖሊሲ አውጭዎች፣ ለተመራማሪዎች እና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረውም አቶ ኡስማን አንስተዋል።
የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ታደለ ልይለት መረጃ የማረጋገጥ ተግባሩ መንግሥት እያካሄደ ያለውን ሁሉን አቀፍ ሪፎርም እውን ለማድረግ የሚያስችል ነው ብለዋል።
መረጃ ሠብሣቢዎች ወደ ሥራ ሢሠማሩም በየደረጃው የሚገኙ ተቋማት እና ግለሰቦች ተገቢውን ትብብር ማድረግ እንደሚገባ ኀላፊው አሳስበዋል።
ከኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የኮምቦልቻ ሥልጠና ማዕከል አሥተባባሪ ወርቅነህ ወልደ ጊዮርጊስ መረጃ የመሠብሠብ ሂደቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሚካሄድ ገልጸዋል።
የሁሉንም የመንግሥት ሠራተኞች መረጃ ዲጂታላይዝድ በማድረግ በሲቪል ሰርቪስ ተቋማት ያሉ ክፍት የሥራ መደቦች ተለይተው ስለሚታወቁ ለሀገሪቱ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንደሚሰጥ አስረድተዋል።
አሚኮ ያነጋገራቸው የሥልጠናው ተሳታፊዎች ሥልጠናው ወደ ሥራ በሚሰማሩበት ወቅት የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች ለማለፍ ያግዘናል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ አንተነህ ፀጋዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
