
ባሕር ዳር፡ የካቲት 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ የተከናወነው የኢኮኖሚ ማሻሻያ የሀገር ኢኮኖሚ አሠራር መሠረታዊ መዋቅሮችን በማሻሻል ኢኮኖሚን ወደ ዘላቂ ውድድር መር እና ተስማሚ ተቋማዊ ሥርዓት ማሸጋገር የሚል ጽንሰ ሀሳብ እንዳለው ይነገራል። ማክሮ ኢኮኖሚን ማረጋጋት፣ መዋቅራዊ ማሻሻያ ማድረግ እና ተቋማዊ አቅምን የማጠናከር ዋና ዋና ዓላማዎችንም ይዟል።
ከዚህ በፊት የነበረው መንግሥት መር የዕድገት ሞዴል የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባትን ጨምሮ የተለያዩ ችግሮች ያሉበት ስለነበር ማሻሻያውን ማድረግ እንዳስፈለገም ተገልጿል። ከዚህ አኳያ ማሻሻያው በመሠረታዊነት የኢኮኖሚ ዕድገት እና መረጋጋት ለማምጣት የተደረገ እንደኾነም ነው የሚነገረው።
የቢዝነስ ፋይናንስ እና ኢኮኖሚክስ አማካሪ እና ተመራማሪው ረዳት ፕሮፌሰር መሠረት ሞላ (ዶ.ር) ማሻሻያው የገንዘብ ማስተካከያን ብቻ ሳይኾን የምጣኔ ሃብት ፍልስፍና ለውጦችን ተከትሎ የተተገበረ መኾኑን ገልጸዋል።
ሪፎርሙ ወደተግባር ከገባ ወዲህ በግብርና፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም፣ በኢንዱስትሪ እና አገልግሎት ዘርፎች ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ለውጦችን አምጥቷል ብለዋል።
የኢኮኖሚ ማሻሻያው የምንዛሬ ሥርዓቱን ነጻ በማውጣት፣ በወለድ ላይ የተመሠረተ የገንዘብ ፖሊሲ በመዘርጋት እና የውጭ ባንኮች እንዲገቡ በመፈቅድ በፋይናንስ ዘርፉ ለውጥ ማምጣቱንም ጨምረዋል።
በዚህም የውጭ ምንዛሬ ክምችት እንዲጨምር፣ የመንግሥት ቀጥታ የባንክ ብድር እንዲቆም እና ወደውጭ የሚላክ ምርት እንዲጨምር አስችሏል ነው ያሉት።
የጸጥታ ችግሮች፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና የግብዓት ዋጋ መናር የማሻሻያው ተግዳሮቶች እንደኾኑ እና የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ ጠቅሰዋል።
ዶክተር መሠረት በማሻሻያው አተገባበር አወንታዊ ለውጦች መጥተዋል ብለዋል። የመዋቅር ችግር በትክክል መለየቱ፣ የግሉ ዘርፍ መጠናከሩ፣ የፋይናንስ ሥርዓት እየተሻሻለ መምጣቱንም በማሳያነት አንስተዋል።
የዋጋ ንረት በፍጥነት አለመቀነስ እና የማኅበራዊ ጫናዎች በየጊዜው እየጨመሩ መኾናቸው በማሻሻያው አተገባበር የታዩ ክፍተቶች መኾናቸውን አማካሪው አንስተዋል። ማሻሻያው በሂደት ላይ በመኾኑ የዋጋ ግሽበት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ፣ የድጋፍ መርሐግብሮችን በማስፋፋት፣ የሪፎርም ቅደም ተከተል ጥራት በማሻሻል ክፍተቱን መሙላት እንደሚገባም ነው የመከሩት።
የፖሊሲ ኮምኒኬሽን ሥራን ማሳደግ በማሻሻያው ትኩረት ሊደረግበት የሚገባ ጉዳይ ነው ያሉት ተመራማሪው በማሻሻያው የተገኘውን ለውጥ፣ የተቀመረውን አሠራር እና መሰል ጉዳዮች ላይ ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ መፍጠር ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ጠቁመዋል።
እንደ ረዳት ፕሮፌሰር መሠረት ገለጻ የኢኮኖሚ ማሻሻያው በቴክኒክ ደረጃ ትክክለኛ ነው።ነገር ግን ስኬቱ የሚወሰነው በፖለቲካ መረጋጋት፣ በማኅበራዊ ተቀባይነት እና በተቋማዊ ብቃት ነው። የመንግሥት ተቋማትም ማሻሻያውን ለማሳካት መሠረታዊ ናቸው። የሕግ የበላይነት፣ የመንግሥት ቁርጠኝነት፣ ሰላም እና መረጋጋትም ወሳኝ መኾናቸውን አስገንዝበዋል።
የኢኮኖሚ ማሻሻያው በአግባቡ ከተመራ የረጅም ጊዜ ዕድገት እንደሚያመጣም አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!!
