‎የሁለት ጊዜ የኦሎምፒክ ሻምፒዮኗ ቢያትሪስ ቼቤት ወደ ኢትዮጰያ ልትመጣ ነው።

0
50

የሁለት ጊዜ የኦሎምፒክ ሻምፒዮኗ ቢያትሪስ ቼቤት በኢትዮጵያ ታላቁ ሩጫ ላይ በክብር እንግድነት እንደምትገኝ አዘጋጆቹ ይፋ አድርገዋል፡፡

የዓለም አትሌቲክስ ድምቀት የኾነችው እና የሁለት ጊዜ የኦሎምፒክ ሻምፒዮኗ ኬንያዊቷ አትሌት ቢያትሪስ ቼቤት፣ በመጪው እሑድ ኅዳር 13/2019 ዓ.ም. በሚካሄደው ታላቁ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር ላይ በክብር እንግድነት በአዲስ አበባ እንደምትገኝ ታውቋል፡፡

በባንክ ኦፍ አሜሪካ ስፖንሰር የተደረገው የዘንድሮው የ“ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ” ዓለም አቀፍ ትኩረትን ከፍ ባለ ሁኔታ ያገኘ ሲኾን፣ በረጅም ርቀት የኢትዮጰያውያን ተፎካካሪ የኾነችው ኬንያዊቷ ቢያትሪስ ቺቤት በዚህ መድረክ መገኘቷ ለውድድሩ ተሳታፊዎች እና ለስፖርቱ አፍቃሪ ማኅበረሰብ ትልቅ መነቃቃትን ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።

በተጨማሪም የውድድሩን ዓለም አቀፋዊ ገጽታ ከፍ በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚናን የሚወጣ ነው፡፡ የዓለም ስመ-ጥር አትሌቶች በኢትዮጵያ መድረኮች ላይ መገኘታቸው ውድድሩ ዓለም አቀፍ ትኩረት እንዲያገኝ እና የስፖርት ቱሪዝም እንዲሁም የስፖርት ዲፕሎማሲ እንዲያድግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል።

በአትሌቲክስ ታሪክ ውስጥ የማይረሱ ድሎችን ያስመዘገበችው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ አድናቆትን የተቸረችው ቼቤት በዕለቱ ከሯጮች ጋር በመኾን ዝግጅቱን እንደምትታደም እና አሸናፊዎችን እንደምትሸልም ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ እና የኬንያ የአትሌቲክስ ፉክክር እና ወዳጅነትን ያጠናክራል ተብሎ የተጠበቀው ይህ ጉብኝት በስፖርቱ ዓለም ልዩ ትኩረት አግኝቷል።

#አሚኮ #ስፖርት🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ኅዳር_09_2019_ዓ_ም

በሐናማርያም መስፍን

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here