ከአፍሪካ ቦትስዋና እጩ የኾነችበት የዓለም አትሌቲክስ ሽልማት።

0
34

የዓለም አትሌቲክስ ከ11 ቀናት በኋላ በፈረንሳይ ሞናኮ በሚያከናውነው የሽልማት መድረክ ከሚያከናውናቸው ዘርፎች መካከል አንዱ «የዓመቱ ምርጥ አባል ፌዴሬሽን» ሽልማት ነው። ለ2026 ዓመትም 6 የመጨረሻ እጩዎች ይፋ ሲኾኑ፣ ከአፍሪካ ቦትስዋና በብቸኝነት ተካታለች።

ባከናወኗቸው ተግባራት ድንቅ ውጤት ያስመዘገቡ እና በውጤቱም የስፖርቱን ዕድገት እና ገጽታ ከፍ ለማድረግ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ያበረከቱ አባል ፌዴሬሽኖችን ለማክበር የሚዘጋጀው ይህ ሽልማት፤ ከአፍሪካ፣ ከደቡብ አሜሪካ፣ ከሰሜን እና መካከለኛው አሜሪካ፣ ከእውሮፓ፣ ከኤዢያ እንዲሁም ከኦሺኒያ የተወከሉ ሀገራት ለእጩነት እንዲበቁ አድርጓል።

በአፍሪካ ምድር ስኬታማ መድረኮችን በማዘጋጀት እና በስፖርቱ እድገት ትልቅ ሚና በመጫወት ላይ የምትገኘው ደቡብ አፍሪካዊቷ ሀገር ቦትስዋና ለዚህ ታላቅ ዕውቅና በቅታለች።

የቦትስዋና አትሌቲክስ ማኅበር ከሀገሪቱ መንግሥት ጋር በመተባበር ዓለም አቀፍ ዝግጅቶችን የማስተናገድ አቅሙ እያደገ መምጣቱን፤ ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ በተከናወነው የ2026 የዓለም የዱላ ቅብብል (World Relays) ውድድር ላይ በተግባር አሳይቷል።

እንደ ኮሊን ኬቢትናሺቢ፣ ሌትስሌ ቶቦጎ እና ባያፖ ንዶሪ የመሳሰሉ አትሌቶች ደግሞ በተለያዩ መድረኮች ድንቅ ውጤቶችን ማስመዝገብ ችለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ለመጀመሪያ ጊዜ በተከናወነው የአልቲሜት ሻምፒዮና ላይ ስኬታማ ከመኾናቸው ባሻገር፣ የወጣቶች እና ታዳጊዎች እድገት ላይ ትኩረት አድርገው የሚሠሩ ፕሮጀክቶች መኖራቸው እና የጉዟቸው ቀጣይነት የተረጋገጠ መኾኑን ለዓለም አሳይተዋል።

እነዚህ አፈጻጸሞች ለስፖርተኞቹ፣ ስፖርቱን ለሚከታተሉ አካላት እና ከሀገሪቱ መሪዎች የተሰጠው ከፍ ያለ ትኩረት እንዲሁም ዓለም አቀፍ እውቅና ለቦትስዋና አትሌቲክስ ተጨማሪ ጉልበት ኾኖ ስሟን ከፍ አድርጎታል።

በ2026 የቦትስዋና አትሌቲክስ ማኅበር በአፍሪካ ምድር ላይ የመጀመሪያ የኾነውን የዓለም አትሌቲክስ ሪሌይ ውድድር በስኬት ማስተናገዱ የሚታወስ ሲኾን፣ በቀጣይም የ2028 የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮናን የማስተናገድ ዕድል አግኝቷል።

የቦትስዋና አትሌቲክስ ማኅበር ስኬት የከፍተኛ ደረጃ ውጤቶች እና ዝግጅቶችን የመምራት አቅም እንዲሁም መሰረታዊ እና ወጣቶች ሥልጠናዎችን፣ የአትሌቶች ደኅንነት እና የንግድ አጋርነቶችን የማጠናከር ሁለንተናዊ አቅም ድምር ውጤት ነው።

የዓለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለሽልማት አሸናፊነት የሚጠቀምባቸው ዋና ዋና መስፈርቶች ውስጥ አትሌቶች በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ያስመዘገቧቸው ድንቅ ውጤቶች እና ሜዳሊያዎች፣ ትላልቅ ውድድሮችን የማስተናገድ አቅም፣ የወጣቶች ስፖርት ልማት፣ የአሠልጣኞች እና የአትሌቶችን ደኅንነት እና መብቶች መጠበቅ፣ ፌዴሬሽኖች ጠንካራ የንግድ አጋርነቶችን በመፍጠር እና ግልጽ የአሥተዳደር ሥርዓት በመዘርጋት ስፖርቱን በዘላቂነት መምራት መቻል ይጠቀሳሉ፡፡

ከደቡብ አሜሪካ አርጀንቲና፣ ከሰሜን አሜሪካ አሜሪካ፣ ከአውሮፓ ጣሊያን፣ ከኤዢያ ደቡብ ኮሪያ እንዲሁም ከኦሺኒያ ኒው ዚላንድ ለምርጥ አባል ፌዴሬሽን ሽልማት እጩ የኾኑ ሌሎች ሀገራት ናቸው፡፡

በመጪው ኅዳር 28 አሸናፊው በፈረንሳይ ሞናኮ ይፋ ይኾናል፡፡

ከዚህ ቀደም በተደረጉ የሽልማት መድረኮች በ2025 ቻይና፣ በ2024 አሜሪካ እና በ2023 አውስትራሊያ አሸናፊ በመኾን ዓመቱን አጠናቅቀዋል፡፡

#አሚኮ #ስፖርት🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ኅዳር_09_2019_ዓ_ም

በሐናማርያም መስፍን

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here