የአፍሪካ ዋንጫ 4ኛ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች ሲጠናቀቁ ስድስት ሀገራት ኬኒያ፣ ታንዛኒያ እና ዩጋንዳ በጥምረት ለሚያዘጋጁት ውድድር ማለፋቸውን አረጋግጠዋል።
ከምድብ አንድ ሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር ሞሮኮ ያደረገቻቸውን አራት ጨዋታዎች በሙሉ በማሸነፍ በ12 ነጥብ የአፍሪካ ዋንጫ ትኬቷን ቆርጣለች።
ሞሮኮ በአራተኛ የምድብ ጨዋታ ትናንት ኒጀርን ከሜዳዋ ውጭ 1 ለ 0 ካሸነፈች በኋላ ለ2027ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ማለፏን አረጋግጣለች።
ሞሮኮ በ12 ነጥብ ማለፏን ባረጋገጠችበት ምድብ አንድ ጋቦን በስድስት ነጥብ ሁለተኛ፣ ኒጀር እና ሌሴቶ ደግሞ በሦሥት ነጥብ ሦሥተኛ እና አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
የመጨረሻ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች በመጋቢት ወር ሲካሄዱ ሦሥቱ ሀገራት ሞሮኮን ተከትሎ ለማለፍ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።
በምድብ ስድስት ቡርኪናፋሶ ትናንት ሞሪታኒያን በሜዳዋ 3 ለ 1 ከረታች በኋላ ለ2027ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ማለፏን ያረጋገጠች ሌላኛዋ ሀገር ነች።
ከትናንቱ ድል በኋላ ነጥቧን 10 ያደረሰችው ቡርኪናፋሶ ለቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ ማለፏን አረጋግጣለች።
ከዚሁ ምድብ ስድሰት ባሳለፍነው ሰኞ ማዕከላዊ አፍሪካን 1 ለ 0 ያሸነፈችው ቤኒን በእኩል 10 ነጥብ የአፍሪካ ዋንጫ ማለፏን ስታረጋግጥ ሞሪታንያ ሦሥት መካከለኛው አፍሪካ ደግሞ ያለምንም ነጥብ ከምድቡ ወድቀዋል። የዚህ ምድብ ቀጣይ ሁለት ጨዋታዎችም ለመርሐ ግብር ሟሟያ ብቻ የሚደረጉ ይኾናል።
በምድብ ሰባት ትናንት በተደረገ ጨዋታ ኮሞሮስ ኮንጎን ከሜዳዋ ውጭ 2 ለ 0 ያሸነፈች ሲኾን ይህም ካሜሮን ሀሉት ጨዋታ እየቀራት ለአፍሪካ ዋንጫው እንድታልፍ አድርጓታል።
ኮሞሮስ ከትናንት ድሏ በኋላ ነጥቧን ሰባት በማድረስ ለአፍሪካ ዋንጫ የማለፍ ዕድሏን ስታሰፋ የኮሞሮስ ውጤት ሰኞ እለት ናሚቢያን 3 ለ 0 ያሸነፈችውን ካሜሩን በ10 ነጥብ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፏን እንድታረጋግጥ አድርጓል።
ምድብ 11 ትናንት ሩዋንዳን 2 ለ 0 ያሸነፈችው ማሊ በ10 ነጥብ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፏን አረጋግጣለች። በዚሁ ምድበረ ላይቤሪያ ትናንት ኬፕ ቨርዴን 2 ለ 0 በማሸነፍ በማጣሪያው የመጀመሪያ ድሏን አስመዝግባለች።
ማሊ ማለፏን ባረጋገጠችበት ምድብ 11 ሩዋንዳ በስድስት ነጥብ 2ኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ ኬፕ ቬርዴ እና ላይቤሪያ እኩል ሦሥት ነጥብ አላቸው።
በምድብ 10 ሞዛምቢክ ትናንት ባሕር ዳር ላይ ኢትዮጵያን 1 ለ 0 ካሸነፈች በኋላ ሰኞ ለት ሱዳንን 4 ለ 2 ያሸነፈችው ሴኔጋል በ10 ነጥብ ለአፍሪካ ዋንጫው እንድታልፍ አድርጓል።
ሴኔጋል ማለፏን ባረጋገጠችበት ምድብ 10 ሞዛምቢክ በሰባት ነጥብ 2ኛ፣ ኢትዮጵያ እና ሱዳን ደግሞ በእኩል ሦሥት ነጥብ 3ኛ እና 4ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
ባጠቃላይ ከ4ኛ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች በኋላ ስድስት ሀገራት ሞሮኮ፣ ቤኒን፣ ቡርኪናፋሶ፣ ካሜሩን፣ ሴኔጋል እና ማሊ ለ2027ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል።
ኬንያ፣ ታንዛኒያ እና ኡጋንዳ አዘጋጅ በመኾናቸው በቀጥታ የውድድሩ ተካፋይ ይኾናሉ።
በባዘዘው መኮንን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!



