የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌዴሬሽን/ካፍ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የአፍሪካ ዋንጫ በቀድሞው ቅርፅ ወይም በየሁለት ዓመቱ እንዲካሄድ በሙሉ ድምፅ ወስኗል።
ቀደም ሲል በጥቅምት ወር መጀመሪያ በኬፕ ቨርዴ በተካሄደው የካፍ ስትራቴጂ ኮንፈረንስ የካፍ ስራ አስፈፃሚ ባለፈው ዓመት የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር በየአራት ዓመቱ እንዲካሄድ የወሰነውን ውሳኔ እንደገና እንደሚገመግም እና እንደሚያጤነው የካፍ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፓትሪስ ሞትሴፔ መናገራቸው ይታወሳል።
አሁን እየተካሄደ ያለውን የአፍሪካ ዋንጫ ይተካል ተብሎ የሚጠበቀው አዲሱ የአፍሪካ ብሔራዊ ቡድኖች ሊግን (Africa Nations League) ለማካሄድና በቂ የገንዘብ አቅም ለመፍጠር ብዙ ዓመታት እንደሚያስፈልጉ ካፍ ገልጿል።
የአፍሪካ እግር ኳስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና በራሱ የሚተዳደር ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግም የአፍሪካ ዋንጫ በየሁለት አመቱ እንዲካሄድ ካፍ መወሰኑን ነው የገለፀው።
የካፍ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፓትሪስ ሞትሴፕ የአፍሪካ እግር ኳስ እድገትን፣የካፍ 54 አባል ማህበራት ፍላጎትን እንዲሁም ከአፍሪካ ውጭ ባሉ የእግር ኳስ ክለቦች የሚጫወቱ አፍሪካዊ ተጫዋቾችን ታሳቢ በማድረግ የአፍሪካ ዋንጫ በየሁለት አመቱ እንዲካሄድ ተወስኗል ብለዋል።
በ2027 በኬኒያ፣ታንዛኒያና ኡጋንዳ አስተናጋጅነት የሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ እጅግ ስኬታማ እንደሚሆን እርገጠኛ ነኝ ሲሉም ፕሬዝዳንቱ ገልፀዋል።
ቀጣዮቹ የአፍሪካ ዋንጫዎችን ደግሞ በ2028፣ 2031 እና 2033 ይካሄዳሉ።
ኢትዮጵያ የ2028ቱን የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት ይፋዊ ጥያቄ ያቀረበች ሲሆን የካፍ ቴክኒካል ገምጋቢ ቡድን ከሰሞኑ የኢትዮጵያን መሰረተ ልማቶች በተለያዩ ከተሞች ተዟዙሮ መመልከቱ ይታወሳል።
ባዘዘው መኮንን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!



