የአፍሪካ ዋንጫ በየሁለት ዓመቱ እንዲካሄድ ካፍ ወስኗል።

0
77
‎የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌዴሬሽን/ካፍ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የአፍሪካ ዋንጫ በቀድሞው ቅርፅ ወይም በየሁለት ዓመቱ እንዲካሄድ በሙሉ ድምፅ ወስኗል።
‎
‎ቀደም ሲል በጥቅምት ወር መጀመሪያ በኬፕ ቨርዴ በተካሄደው የካፍ ስትራቴጂ ኮንፈረንስ የካፍ ስራ አስፈፃሚ ባለፈው ዓመት የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር በየአራት ዓመቱ እንዲካሄድ የወሰነውን ውሳኔ እንደገና እንደሚገመግም እና እንደሚያጤነው የካፍ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፓትሪስ ሞትሴፔ መናገራቸው ይታወሳል።
‎
‎አሁን እየተካሄደ ያለውን የአፍሪካ ዋንጫ ይተካል ተብሎ የሚጠበቀው አዲሱ የአፍሪካ ብሔራዊ ቡድኖች ሊግን (Africa Nations League) ለማካሄድና በቂ የገንዘብ አቅም ለመፍጠር ብዙ ዓመታት እንደሚያስፈልጉ ካፍ ገልጿል።
‎የአፍሪካ እግር ኳስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና በራሱ የሚተዳደር ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግም የአፍሪካ ዋንጫ በየሁለት አመቱ እንዲካሄድ ካፍ መወሰኑን ነው የገለፀው።
‎
‎የካፍ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፓትሪስ ሞትሴፕ የአፍሪካ እግር ኳስ እድገትን፣የካፍ 54 አባል ማህበራት ፍላጎትን እንዲሁም ከአፍሪካ ውጭ ባሉ የእግር ኳስ ክለቦች የሚጫወቱ አፍሪካዊ ተጫዋቾችን ታሳቢ በማድረግ የአፍሪካ ዋንጫ በየሁለት አመቱ እንዲካሄድ ተወስኗል ብለዋል።
‎
‎በ2027 በኬኒያ፣ታንዛኒያና ኡጋንዳ አስተናጋጅነት የሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ እጅግ ስኬታማ እንደሚሆን እርገጠኛ ነኝ ሲሉም ፕሬዝዳንቱ ገልፀዋል።
‎
‎ቀጣዮቹ የአፍሪካ ዋንጫዎችን ደግሞ በ2028፣ 2031 እና 2033 ይካሄዳሉ።
‎
‎ኢትዮጵያ የ2028ቱን የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት ይፋዊ ጥያቄ ያቀረበች ሲሆን የካፍ ቴክኒካል ገምጋቢ ቡድን ከሰሞኑ የኢትዮጵያን መሰረተ ልማቶች በተለያዩ ከተሞች ተዟዙሮ መመልከቱ ይታወሳል።
‎
ባዘዘው መኮንን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here