የኤም ዋይ ዜድ የእግር ኳስ ክለብ በተለያዩ የዕድሜ ክልል ያሉ ታዳጊዎችን እያሠለጠነ ብቁ ስፖርተኞችን እያፈራ ይገኛል።
በ2014 ዓ.ም በፍኖተሰላም ከተማ ታዳጊዎችን ከአልባሌ ቦታ ለመታደግ የተመሠረተው የኤም ዋይ ዜድ የእግር ኳስ ክለብ ጠንካራ ሥልጠናዎችን እየሰጠ ይገኛል።
ተጫዋቾቹ በትርፍ ጊዜያቸው በሚከታተሉት ሥልጠና አቅማቸውን እያሻሻሉ እና ህልማቸውን እውን ለማድረግ እየጣሩ መኾናቸውን ገልጸዋል።
የክለቡ አሠልጣኝ ይታይህ ላቀ እንደተናገረው ክለቡ ከ13፣ ከ15 እና ከ17 ዓመት በታች እንዲሁም ከ17 ዓመት በላይ የዕድሜ ክልል ሥልጠናዎችን በመስጠት ታዳጊዎችን ወደተለያዩ ክለቦች መቀላቀል ችሏል።
በዞን አቀፍ ውድድሮችም ውጤታማ በመኾን ለአማራ ሊግ መብቃት ችሏል፤ ኾኖም የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ እጥረት ለሥልጠናው ዋና ማነቆ ኾኗል ነው ያለው።
የፍኖተሰላም ከተማ አሥተዳደር ባሕል ቱሪዝም እና ስፖርት ጽሕፈት ቤት የስፖርት ዘርፍ ቡድን መሪ ዘላለም ደምሴ በበኩላቸው ጤናማ ማኅበረሰብ ለመገንባት በወጣቶች ላይ ሰፊ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
ክለቦች ውጤታማ እንዲኾኑ የድጋፍ እና ክትትል ሥራዎች እየተከናወኑ ሲኾን ያጋጠመውን የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታ ችግር ለመፍታት ኅብረተሰቡን እና ባለሀብቶችን ያሳተፈ ጥረት እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡ ንጉስ ስንታየሁ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!



