አዲስ አበባ፡- 17/02/19 (አሚኮ) – የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ከስፖርት ማህበራትና ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያደረገ ነው።
የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር አክሊሊ ታደሰ (ዶ/ር)፣ የስፖርት ማህበራት ለኢትዮጵያ የስፖርት ልማት ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል። መንግስት ስፖርቱን ለሁለንተናዊ ሀገራዊ እድገትና ግንባታ ለመጠቀም የፖሊሲና የአደረጃጀት ማሻሻያዎች ማድረጉን የገለፁት ሚኒስትሩ፣ የተያዘው ግብ እንዲሳካ የስፖርት ማህበራት ድርሻ ቀዳሚ መሆኑን ገልፀዋል።
መንግስት ስፖርትን ከውድድርና መዝናኛነት ባለፈ ለሀገራዊ እድገትና ዲፕሎማሲ መሰረት እንዲሆን አቅዶ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
በወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መክዩ መሃመድ ፣ የስፖርቱን አቅም ለመጠቀምና የተያዘውን ሀገራዊ ተልዕኮ ለማሳካት ተቋሙ በአዲስ መደራጀቱን አንስተዋል።
በመድረኩ “ኢትዮጵያዊ የስፖርት ማህበር ግንባታ ከታሪክ ወደ ተፅዕኖ” በሚል ርዕስ መነሻ ፁሁፍ ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ይገኛል።



