የቀድሞው የሊቨርፑል ኮከብ እና የግብጽ ብሔራዊ ቡድን አጥቂ ሞሐመድ ሳላህ በእንግሊዝ ለስድስት ወራት መኪና እንዳያሽከረክር እገዳ ተጥሎበታል። በተጨማሪም የገንዘብ ቅጣትም ተወስኖበታል።
ባለፈው መጋቢት ወር በቼሻየር ዊልምስሎው አካባቢ የሳላህ መኪና በሰዓት 30 ማይል በኾነው የፍጥነት ወሰን ላይ በ36 ማይል ሲያሽከረክር በፍጥነት መቆጣጠሪያ ካሜራ ተቀርጿል።
ሳላህ መኪናውን በወቅቱ ማን ያሽከረክረው እንደነበር ለፖሊስ አካላት መረጃ ባለመስጠቱ እና ለቀረበለት የክስ ጥሪ ምላሽ ባለመስጠቱ ፍርድ ቤት በሌለበት ጥፋተኛ ብሎታል።
በክርክሩ የቀረበበት የፍጥነት ወሰን ማለፍ በወቅቱ እሱ አለመኾኑ ተረጋግጦ ክሱ የተነሳ ቢኾንም አሽከርካሪውን አለማሳወቅ በሚለው ጥፋት ተቀጥቷል።
የእንግሊዝ ፍርድ ቤት ከ6ወር የማሽከርከር እገዳ በተጨማሪ ሳላህ 1ሺህ 44 ፓውንድ እንዲከፍል ውሳኔ አስተላልፏል።
ይህ እገዳ በእንግሊዝ ግዛት ውስጥ ብቻ የሚጸና በመኾኑ በቱርኩ ክለብ ለሚገኘው ሳላህ ለእግር ኳስ እንቅስቃሴው እንቅፋት ላይኾንበት እንደሚችል ተጠቁሟል ሲል ዘጋርዲያን አስነብቧል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!



