‎ናይሮቢ እንዴት ለንደንን አሸነፈች?

0
157
የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በየሁለት ዓመቱ የሚካሄድ የአትሌቲክሱ የዓለም ዋንጫ ነው፡፡ ይህን ውድድር በአፍሪካ አህጉር ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲካሄድም ኬኒያ ተመራጭ ሀገር ኾናለች፡፡
ምሥራቅ አፍሪካዊቷ ጎረቤታችን እና የረዥም ርቀት ተፎካካሪያችን ኬንያ ይህንን ዕድል እንዴት አገኘች የሚለው ትኩረት የሳበ ጉዳይ ኾኗል፡፡
የሀገሪቱ ዋና ከተማ ናይሮቢ የእንግሊዟን ለንደን በመብለጥ ጭምር ነው ታላቁን ውድድር ለማስተናገድ የተመረጠችው፡፡
ኬኒያ ያለፈውን የ2025ቱ የዓለም ሻምፒዮና ለማስተናገድ ጥያቄ አቅርባ በቶኪዮ ብትበለጥም ለ2029 ግን ጠንካራ እና አሳማኝ ዝግጅት በማቅረብ ማሸነፍ ችላለች።
ውድድሩ 48 ሺህ ተመልካቾችን የመያዝ አቅም ባለው እና ሙሉ እድሳት በተደረገለት በሞይ ዓለም አቀፍ ስፖርት ማዕከል ካሳራኒ ስታዲየም ይካሄዳል።
ስታዲየሙ ኬንያ ከታንዛኒያ እና ኡጋንዳ ጋር በጋራ ለምታስተናግደው የ2027ቱ የአፍሪካ ዋንጫ እየተገነባ በመኾኑ አዲስ የውድድር መም፣ ዘመናዊ የመብራት ሥርዓት፣ የተሻሻሉ የተጫዋቾች መቀያየሪያ ክፍሎች እና የሚዲያ ማዕከላትን ጨምሮ ሙሉ መዋቅራዊ እድሳት ተደርጎለታል፡፡
ከዋናው ስታዲየም በተጨማሪ ታዋቂው ኛዮ ብሔራዊ ስታዲየም አትሌቶች ከፍተኛ የልምምድ ዕቅዳቸውን የሚያከናውኑበት ዋና የልምምድ ስፍራ ሆኖ ተለይቷል።
ናይሮቢ የ2029ኙን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አፍሪካ ለማምጣት ያደረገችው ዝግጅት በመንግስት ከፍተኛ ድጋፍ እና በጠንካራ መሠረተ ልማት ግንባታ ላይ የተመሠረተ ነው።
ኬንያ ከዚህ ቀደም የ2017ቱን የዓለም ከ18 ዓመት በታች እና የ2021ዱን የዓለም ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎችን በብቃት ማስተናገዷ የአሁኑን ትልቅ ውድድር ለማስተናገድ እንደ ትልቅ መነሻ ተወስዷል።
በሰይድ ኢብራሂም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here