ለአሸናፊዎቹ የተዘጋጁት ዋንጫዎች።

0
118
ከሁሉ የተሻለው ብቻ አሸናፊ የሚኾንበት እና የሚሸለምበት የዓለም አትሌቲክስ አዲሱ ውድድር አልቲሜት ሻምፒዮና።
የዓለም አትሌቲክስ ለአሸናፊዎቹ የተዘጋጁትን ዋንጫዎች ይፋ አድርጓል፡፡
አልቲሜት ላይ ሁሉም አሸናፊ በተለየ ሁኔታ የተዘጋጀውን ዋንጫ አያገኝም፡፡ ይልቁኑም ከተለመደው አሠራር ወጣ በማለት ከምርጦቹ የተሻለው ምርጥ ብቻ በልዩ ሁኔታ የተዘጋጀውን ዋንጫ አሸናፊ ይኾናል፡፡
በሀንጋሪ ቡዳፔስት ሊጀመር በመላው ዓለም በጉጉት የሚጠበቀው የአልትሜት ሻምፒዮና ከተለመደው የሜዳሊያ ሥርዓት ወጣ ባለ መልኩ አትሌቶች የሚወዳደሩት ለዋንጫ ብቻ እንደሚኾን ተገልጿል።
የዓለም አትሌቲክስ ፕሬዝዳንት ሴባስቲያን ኮ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ለሚወጡ አሸናፊዎች ሜዳሊያዎችን መስጠት ከውድድሩ ዋና ጽንሰ-ሀሳብ ጋር አይሄድም ሲሉ ከብዙ አሸናፊዎች መካከል የተሻለው ብቻ ድል ሲያደርግ ውድድሩ ግቡን ይመታል ብለዋል።
ሁሉም ተሳታፊ አትሌቶች ስማቸው ከውጭ የውድድሩ ስም ደግሞ ከውስጥ በኩል ተቀርጾባቸው የተዘጋጁ ልዩ የእጅ አምባር ይበረከትላቸዋል።
አሸናፊዎች የሚቀበሉት የሻምፒዮናውን ኮከብ አርማ የያዘው ዋንጫ ሙሉ የሚኾነው በተለየ ሁኔታ በተነደፈለት ሂደት ነው፡፡
በዋንጫው ላይ የሚገኘው ልዩ ክፍተት ወይም ቀዳዳ አሸናፊው የራሱን አምባር ሲያስገባበት ብቻ ዋንጫው ሙሉ እንዲኾን ተደርጎ ነው የተሠራው፡፡
ይሄም የውድድሩ አዘጋጅ በኾነችው ሃንጋሪ ዲዛይነሮች በዕደ-ጥበብ የተሠራ ሲኾን ይህ ንድፈ ሀሳብ የቀረበውም በአሜሪካዊው የኦሎምፒክ ሻምፒዮን እና የመድረኩ የፈጠራ ሥራዎች አማካሪ በኾነው አሜሪካዊው ኖህ ላይልስ ነው።
የሽልማት አሰጣጡም አዲስ መልክ ያለው ሲኾን አትሌቶች ድል ካደረጉ በኃላ በቀጥታ በመድረኩ በተዘጋጀላቸው ቦታ የተዘጋጀላቸውን ዋንጫ እራሳቸው አንስተው አሸናፊነታቸውን ያበስራሉ።
ይህ ድል የማድረግ ቅጽበትም በደማቅ ሁኔታ በሙዚቃ እና በርችት ይታጀባል፡፡ አሸናፊዎች የድል ጉዟቸውን አድርገው በስታዲየም ውስጥ ባለው ለሻምፒዮኖች በተዘጋጀው መድረክ አልፈው ከሕዝቡ ጋር አሸናፊነታቸውን ያከብራሉ።
ከፈረንጆቹ መስከረም 11/2026 እስከ መስከረም 13/2026 የሚካሄደው ይህ የመጀመሪያው የዓለም አትሌቲክስ አልቲሜት ሻምፒዮና የዓለም የኦሎምፒክ እና የዲያመንድ ሊግ አሸናፊዎችን ጨምሮ የዓመቱን ምርጥ አትሌቶች የሚያገናኝ ነው፡፡
እንደ የዓለም አትሌቲክስ መረጃ ከኾነ ይህ በጉጉት የሚጠበቀው መድረክም 10 ሚሊዮን ዶላር የሽልማት ገንዘብ ተመድቦለታል።
✍️በሐናማርያም መስፍን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here