የጥበብ ውርስ፤ የሜሲ እና የላሚን ያማል ምትሃታዊ የዕጣ ፈንታ ዑደት

0
153
👑
🏆
ጊዜ እና ዕጣ ፈንታ ምንኛ ድንቅ የጥበብ ሸማኔዎች ናቸው! ከዓመታት በፊት በባርሴሎናው ካምፕ ኑ ስታዲየም አንድ አስገራሚ እና ድብቅ ክስተት ተፈጠረ። ገና ብቅ እያለ የነበረው የ20 ዓመቱ አይነፋር ወጣት ሊዮኔል ሜሲ የአምስት ወር ጨቅላ ሕጻንን በፕላስቲክ ገንዳ ውስጥ ሲያጥብ፤ ያኔ እያጠመቀው የነበረው በውኃ ብቻ ሳይኾን በእግር ኳስ የጥበብ ፀጋም ጭምር ነው መሰል እየተባለ ሲወራ ነበር።
ይህ ድንቅ ትዕይንት የተፈጠረው ከሞሮኮ እና ከኢኳቶሪያል ጊኒ ተሰደው ካታሎኒያ የገቡት የያማል ወላጆች የገንዘብ አቅም ስላልነበራቸው ዩኒሴፍ እና የካታላኑ “ስፖርት” ጋዜጣ ባዘጋጁት የበጎ አድራጎት የእጣ ውድድር ላይ ተሳትፈው ዕድል ቀንቷቸው ነበር።
አሸናፊ በመኾናቸውም የ5 ወር ጨቅላ ልጃቸውን ይዘው በካምፕ ኑ የተጋጣሚዎች መልበሻ ክፍል ሲገኙ ዕጣ ያቀረበችላቸው ከ20 ዓመቱ ሊዮኔል ሜሲ ጋር እንዲጣመሩ ነበር። ያኔ ሜሲ ሕጻኑን እንዴት መያዝ እንዳለበት ግራ ተጋብቶ ፊቱ ሲለዋወጥ የተነሳው የፎቶ ካሜራ ብልጭታ ግን የሁለት ዘመናት የእግር ኳስ አፈ ታሪኮችን ታሪካዊ ትስስር ለዘላለም እያተመ ነበር።
ይህ የዘመናችን የምንግዜም ታላቅ ተጫዋች በዚያን ቀን ሳያውቀው ያስተላለፈው ምትሃታዊ ቡራኬ ያንን ደስተኛ ትንሽ ሕጻን ዛሬ በዓለማችን ላይ ካሉ እጅግ ተጽዕኖ ፈጣሪ እና አስደናቂ የእግር ኳስ ጠበብቶች ተርታ እንዲሰለፍ አድርጎታል።
ያ ጨቅላ ሕጻን የዛሬው አንጸባራቂ ኮከብ ላሚን ያማል ነው። የሜሲን የእግር ኳስ ዱካ በጥብቅ እየተከተለ ከድህነት መንደር ተነስቶ የዓለምን ትኩረት የሳበው ይህ ድንቅ ወጣት የንጉሡን ቡራኬ ወደ ታላቅ ክብር ቀይሮታል።
ዛሬ ደግሞ ያ የተአምር ዑደት ወደ ታሪካዊ ማሳረጊያው ደርሷል። የትናንቱ አጥማቂ እና ተጠማቂ የዛሬዎቹ የእግር ኳስ ነገሥታት ያንን የጠበቀ ትስስር በልባቸው ይዘው፤ ነገር ግን ታላቅ ዋንጫን እርስ በርስ ለመነጣጠቅ ወደ አንድ ሜዳ ይገባሉ።
የትውልዱ ሊቅ እና ተተኪው አልጋ ወራሽ ፊት ለፊት ሲፋጠጡ እጣ ፈንታ የጻፈችው ይህ አፈ ታሪክ በዓለም ፊት ህያው ኾኖ ይቆማል።
ታሪክም ከሕጻን መታጠቢያ ገንዳ እስከ የዓለም ታላላቆች ፍልሚያ የተጓዘውን ይህን ተአምራዊ ገድል በወርቅ ቀለም ይጽፈዋል።
በስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here