የአርጀንቲና አስፈሪ ማጥቃት ወይስ የስፔን የብረት አጥር?

0
119

 

የየየ2026ቱ የፊፋ ዓለም ዋንጫ ፍጻሜ በኒዮርክ-ኒው ጀርሲ ስታዲየም ዛሬ ምሽት 4፡00 ላይ ሲካሄድ በዓለም እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ታሪካዊ ፍልሚያ ይኾናል ተብሎለታል።

ይህ ጨዋታ የአውሮፓ እና የደቡብ አሜሪካ ሻምፒዮናዎችን ከ60 ዓመታት በኋላ በዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ያገናኘ በመኾኑ መላውን ዓለም በጉጉት እንዲጠብቅ አድርጓል። የዛሬውን ጨዋታ ልዩ እና ማራኪ የሚያደርጉት ደግሞ ይህ የፍጻሜ ጨዋታ በዋናነት “የትውልድ ፍልሚያ” ተብሎ ሊገለጽ የሚችል መኾኑ ነው።

የአርጀንቲናው የ39 ዓመት አንጋፋ ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ በታሪኩ የመጨረሻው ሊኾን በሚችለው የዓለም ዋንጫ ላይ ድንቅ ብቃቱን እያሳየ ይገኛል። ሜሲ በዚህ ውድድር በ8 ግቦች እና 4 ግብ የኾኑ ኳሶችን አመቻችቶ በማቀበል የኮከብ ግብ አግቢነቱን ለመውሰድ ዛሬ የሚያደርገው ጨዋታ ወሳኝ ነው።

በሌላ በኩል የስፔኑ የ19 ዓመት ወጣት ድንቅ ተጫዋች ላሚን ያማል ከልጅነት አርዓያው ሜሲ ጋር ፊት ለፊት ይገናኛል። ያማል በዚህ ውድድር ጉዳት አጋጥሞት የነበረ ቢኾንም፣ በስፔን የቀኝ መስመር ማጥቃት ላይ አሁንም ከፍተኛ ብቃት እና ታክቲክ እንዳለው አሳይቷል። ለዛሬው የአርጀንቲና የተከላካይ ክፍል ስጋት እንደሚኾንም ይጠበቃል።

የዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ የሁለት ፍጹም ተቃራኒ ጠንካራ ቡድኖች ፍልሚያ በመኾኑ ጨዋታውን ተጠባቂ አድርጎታል።

አርጀንቲና በውድድሩ 19 ግቦችን መረብ ላይ በማሳረፍ አስፈሪ የአጥቂ መስመር ያላት በመኾኑ የዛሬው ጨዋታ ተጠባቂ ያደርገዋል። ሜሲ፣ ላውታሮ ማርቲኔዝ እና ኤንዞ ፈርናንዴዝ ያሉበት የአርጀንቲና የአጥቂ ክፍል ዛሬም ተአምር ሊሠራ እንደሚችል ነው የሚጠበቀው።

ስፔን በበኩሏ በውድድሩ እስካሁን ያስተናገደችው ግብ ከውድድሩ ዝቅተኛ መኾን ምርጥ ተከላካይ እንደገነባች አመላካች ነው። አይበገሬው የስፔን ተከላካይ ዛሬ የአርጀንቲናን የአጥቂ ክፍል ሊያቆም ይችላል ነው የተባለው።

ጨዋታው የአርጀንቲናው አስፈሪ የማጥቃት መስመር የስፔኑ የተከላካይ የብረት አጥርን ለመስበር የሚደርገው ብርቱ ትግል የጨዋታው ትዕይንት በመኾን በብዙዎች የሚጠበቅ ነው።

በስፔን በኩል አማካዩ ሮድሪ የቡድኑ የልብ ትርታ ነው። በውድድሩ 648 ኳሶችን በማቀበል ቀዳሚ ሲኾን የጨዋታውን ፍሰት በመቆጣጠር ረገድ ትልቅ ሚና አለው። በተጨማሪም ሚኬል ኦያርዛባል በ5 ግቦች የስፔን ከፍተኛ ግብ አግቢ በመኾን የፊት መስመሩን ይመራል።

ሁለቱ ሀገራት በታሪካቸው 16 ጊዜ የተገናኙ ሲኾን እያንዳንዳቸው 6 ጊዜ አሸንፈው 2 ጨዋታዎችን አቻ ተለያይተዋል። በዓለም ዋንጫ መድረክ የተገናኙት አንድ ጊዜ ብቻ ሲኾን በ1966 በነበረው ጨዋታ አርጀንቲና 2 ለ 1 አሸንፋ ነበር።

የኦፕታ ሱፐር ኮምፒውተር የቡድኖቹን የማሸነፍ ግምት ሲያስቀምጥ እንዳለው ስፔን የማሸነፍ ዕድሏ 59 ነጥብ 46 በመቶ ሲኾን ለአርጀንቲና የማሸነፍ ዕድሉን 40 ነጥብ 54 በመቶ ሰጥቷታል።

የስፔኑ አሠልጣኝ ሉዊስ ዴ ላ ፉዌንቴ ስለጫወታው ሲናገሩ ጨዋታው ተሰጥኦ እና እግር ኳሳዊ ውበት የበላይነት የሚይዙበት ይኾናል ነው ያሉት።

#አሚኮ_ዜና #የዓለምዋንጫ_2026 #ስፔን #አርጄንቲና

#ባሕር_ዳር #ሐምሌ12_2018_ዓ_ም

በምስጋናው ብርሃኔ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here