የኢትዮጵያውያን ስኬት በፓሪስ ዳይመንድ ሊግ፤ እና ሌሎች ክብረ ወሰኖች

0
21

 

አዲስ አበባ: ሰኔ 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የዲያመንድ ሊግ ውድድር በ7ኛ ከተማው ትናንት ፓሪስ ላይ ሲከናወን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያዩ ርቀቶች ተሳትፈዋል።

በሴቶች 1 ሺህ 500 ሜትር ሦስት አትሌቶች የተሳተፉ ሲኾን ፍረወይኒ ኃይሉ የራሷን የዓመቱን ፈጣን ሰዓት 3 ደቂቃ ከ55 ሰከንድ ከ92 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት ሁለተኛ ወጥታለች።

በዘንድሮው ዳይመንድ ሊግ በ3 ሺህ ሜትር እና በ5 ሺህ ሜትር በመሳተፍ ድል ያደረገችው አትሌቷ በዚህ ርቀት የተሳተፈችው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ሌሎች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ሀረገወይን ካላዩ 12ኛ አስቴር አረሪ 13ኛ ኾነው ጨርሰዋል።

እንግሊዛዊቷ ጆርጂና ሀንተር ቤል ርቀቱን 3 ደቂቃ ከ55 ሰከንድ ከ63 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት አሸንፋለች።

በሌላኛው ርቀት ተጠባቂው የወንዶች 3ሺህ ሜትር መሰናክል ሲኾን አራት ኢትዮጵያውያን እሌቶች ተካፋይ ኾነዋል።

ከውድድሩ መጀመር አስቀድሞ ትልቅ ግምት ያገኘው ርቀቱ በጀርመናዊው ካርል ቤበንዶርፍ አሸናፊነት ተጠናቅቋል። ቅድመ ግምት ያገኙ አትሌቶች ባልቀረቡበት ርቀት ኢትዮጵያዊው ገመቹ ጎዳና ሁለተኛ ኾኗል።

በዳይመንድ ሊጉ በርቀቱ ስድስተኛ ተሳትፎውን ያደረገው አትሌቱ 8 ደቂቃ ከ05 ሰከንድ ከ86 ማይክሮ ሰከንድ የገባበት ሰዓት ሲኾን የራሱን ፈጣን ሰዓት ያሻሻለበትም ኾኗል።

ኤድመንድ ሴረም ከኬንያ ሦስተኛ ቅድመ ግምት ተሰጥቶት የነበረው ሳሙኤል ፍሬው 4ኛ ኾኖ ጨርሷል። አብርሃም ስሜ 7ኛ እና ኃይለማርያም አማረ 18ኛ ኾነው አጠናቅቀዋል።

በ2023 እዚሁ ቦታ ላይ ለሜቻ ግርማ ያስመዘገበው 7 ደቂቃ ከ52 ሰከንድ ከ11 ማይክሮ ሰከንድ የቦታው ክብረወሰን ኾኖ ይገኛል።

በ5ሺህ ሜትር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከፈጣን ደረጃዎች ውጭ ሲኾኑ አዲሱ ይሁኔ 12ኛ፣ ሀይሪ በጂጋ 15ኛ፣ ጌትነት ዋለ 16ኛ እና ኩማ ግርማ 19ኛ ኾነው ጨርሰዋል።

አዲሱ ይሁኔ በዚህ ርቀት ቀዳሚዎችን ደረጃ ይዞ ባያጠናቅቅም በርቀቱ የነጥብ ፉክክሩን በ16 ነጥብ ይመራል።

በፓሪስ ዳይመንድ ሊግ በዕለቱ ክብረወሰን እና ፈጣን ሰዓቶች የተመዘገቡ ሲኾን በሴቶች 800 ሜትር በተከታታይ መድረኮች ፈጣን ሰዓቶችን ማስመዝገብ የቻለችው ስዊዘርላንዳዊዋ አትሌት አውድሪ ዌሮ አሸንፋለች። ርቀቱን ለማጠናቀቅ 1 ደቂቃ ከ53 ሰከንድ ከ80 ማይክሮ ሰከንድ ወስዶባታል።

በዚህ የነጥብ ፉክክር ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብም የመጀመሪያዋ አትሌት ኾናለች።

ስዊዘርላንዳዊዋ አትሌት አውድሪ ዌሮ በቀኑ 4 ክብረ ወሰኖችን ነው ማስመዝገብ የቻለችው።

እነዚህም የዓመቱ ፈጣን ሰዓት፣ የዳይመንድ ሊግ ክብረወሰን፣ የቦታው ፈጣን ሰዓት እና የሀገሯ ክብረወሰን ናቸው።

ታዲያ አሁን ጥያቄው ክብረ ወሰኑ ከተመዘገበ ረጅም ዓመት ያስቆጠረው የ800 ሜትር ርቀት ሊሰበር እንደሚችል የአትሌቷ ብቃት አመላካች ኾኗል።

በሴቶች 800 ሜትር የዓለም ክብረ ወሰን 1 ደቂቃ ከ53 ሰከንድ ከ28 ማይክሮ ሰከንድ ሲኾን ክብረ ወሰኑን ያስመዘገበችው የቼኮዝሎቫኪያዋ ያርሚላ ክራቶቺቪሎቫ እ.አ.አ በ1983 ነው።

ይህም በአትሌቲክስ ስፖርት ታሪክ ውስጥ በግል የሩጫ ውድድር ዘርፍ ለረጅም ጊዜ ሳይሰበር የቆየ ቀዳሚው የዓለም ክብረ ወሰን ኾኖ ቀጥሏል።

ተሰበረ የሚለውን ዜና የምንሰማበት ጊዜ ሩቅ እንደማይኾንም እሙን ነው።

ከ400 ሜትር ሩጫ እና 400 ሜትር መሰናክል ወደ 800 ሜትር ርቀት ፊቷን ያዞረችው ኔዘርላንዳዊቷ ፌምኬ ብሮደርስ ቦል ሁለተኛ ኾና ስትጨርስ የገባችበት ሰዓት 1 ደቂቃ ከ55 ሰከንድ ከ60 ማይክሮ ሰከንድ ኾኗል። የራሷ ፈጣን የርቀቱ ሰዓቷም ኾኗል።

በዚህ ርቀት በዳይመንድ ሊግ የነጥቡ ፉክክሩ ጽጌ ድጉማ በ14 ነጥብ ከዌሮ በመቀጠል ሁለተኛ ላይ ተቀምጣለች።

በወንዶች 100 ሜትር ኖህ ላይስ ሁለተኛ ሲኾን ከፍተኛ ትንቅንቅ በታየበት በዚህ ርቀት ትራይቨን ብሮምዌል ቀዳሚ በመኾን አጠናቅቋል። ጃኮብስ ማርሴል ሦስተኛ አካኒ ሲምብኔ አራተኛ እና ፈርዲናንድ ኦማንያላ 6ኛ ኾነው ጨርሰዋል።

የዲያመንድ ሊጉ መድረክ ድምቀት ከኾኑት ርቀቶች መካከል የወንዶች 400 ሜትር ቀዳሚው ነው። የዓለም የዱላ ቅብብል ውድድር ሻምፒዮኑ ባለድል ኾኗል።

የ22 ዓመቱ የቦትስዋና ታዳጊ ኮከብ ቡሳንግ ኮለን ኬቢናትሺፒ አስደናቂ እና ያልተጠበቀ ድል በመቀዳጀት የወንዶች 400 ሜትር ውድድርን በሚያስገረም ሰዓት በመግባት አሸንፏል።

ይህ ሰዓትም ሦሥት ክብሮችን ሲያቀዳጀው የራሱን ፈጣን ሰዓት እና የዲያመንድ ሊግ ውድድሩን ክብረወሰን መስበር ብቻ ሳይኾን ማይክል ኖርማን በ2022 የፈረንጆቹ ጊዜ አስመዝግቦት የነበረውን የዳይመንድ ሊግ ክብረወሰን በ43 ሰከንድ ከ60 ማይክሮ ሰከንድ ማሻሻል ችሏል።

በምርኩዝ ዝላይ በቅርቡ የተሞሸረው የስዊድኑ ሙንዶ ዱፕላንትስ 6 ሜትር ከ13 ሴንቲሜትር በመዝለል አሸናፊ ኾኗል። የቦታው ክብረወሰንም ኾኖ ተመዝግቧል።

የዲያመንድ ሊጉ መድረክ ከ6 ቀናት በኋላ በስምንተኛ ከተማው በአሜሪካዋ ዩጅንም ይመለሳል።

#አሚኮ_ዜና #ስፖርት

ዘጋቢ፦ ሐናማርያም መስፍን

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here