ደብረ ብርሃን: ሰኔ 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የስፔኑ ኃያል ክለብ ባርሴሎና የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን አጥቂ እና አምበሉን ሃሪ ኬንን ከዓለም ዋንጫው መጠናቀቅ በኋላ ሙሉ አቅሙን ተጠቅሞ ወደ ካፕኑ ማዛወር ይፈልጋል ተብሏል።
ዕድሜው 32 ዓመት የደረሰው ሃሪ ኬን በተጠናቀቀው የ2025/26 የውድድር ዓመት ለባየር ሙኒክ በ51 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ 61 ግቦችን በማስቆጠር በአውሮፓ እጅግ አስፈሪ ከኾኑ አጥቂዎች መካከል አንዱ መኾኑን በተግባር አስመስክሯል።
ይህንን ድንቅ ብቃቱንም በ2026 ዓለም ዋንጫ ላይ በመድገም በሦሥት የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ ሦሥት ግቦችን ማስቆጠር ችሏል።
ዴይሊ ሜል እንደዘገበው የባርሴሎና ባለሥልጣናት ለተጫዋቹ ያላቸውን የዝውውር ፍላጎት በይፋ ለማሳወቅ ከሃሪ ኬን ወኪል ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት መጀመራቸውን ገልጸዋል።
የካታላኑ ክለብ ባርሴሎና ለተጫዋቹ ዝውውር ከፍተኛ በጀት መድቦ መንቀሳቀስ መጀመሩም ተጠቁሟል።
ኬን ባየር ሙኒክን የሚለቅ ከኾነ ወደ እንግሊዝ በመመለስ አሊን ሽረር በፕሪሚየር ሊጉ ያስመዘገበውን የ260 ግቦች የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ክብረ ወሰንን ለመስበር እንደሚፈልግ ቀደም ሲል በስፖርት ተንታኞች ዘንድ በሰፊው ሲነገር መቆየቱ ይታወሳል።
#አሚኮ_ዜና #ስፖርት
ዘጋቢ፦ ሀብታሙ ዳኛቸው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!



