18 የዓለም ዋንጫዎችን የዘገቡት አንጋፋው ጋዜጠኛ።

0
18

 

ኤንሪኬ ማካያ ማርክኤዝ ይባላሉ በስፖርት ጋዜጠኝነት ዓለም አንጋፋ ናቸው። እኒህ ሰው 18 የዓለም ዋንጫዎችን እንደ ጋዜጠኛ ዘግበዋል። ይህ አስደናቂ ስኬት በአርጀንቲና ዋና አሠልጣኝ ሊዮኔል ስካሎኒ ዕውቅና ተሰጥቶታል።

አርጀንቲና በምድብ መጨረሻ ጨዋታ ከዮርዳኖስ ጋር ከምታደርገው ጨዋታ በፊት በአርሊንግተን በተካሄደው የአርጀንቲና ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ማካያ ማርክኤዝ የመጀመሪያውን ጥያቄ እንዲጠይቁ ተጋብዘው ነበር።

ስካሎኒ ለጥያቄው ምላሽ ከመስጠታቸው በፊት የእኒህን አንጋፋ ጋዜጠኛ አስደናቂ የሥራ ዘመን እና በእግር ኳስ ጋዜጠኝነት ውስጥ የነበራቸውን ዘላቂነት አድንቀዋል።

“ከእርስዎ ጥያቄዎች ለአንዱ ምላሽ መስጠት መቻሌ ለእኔ ትልቅ ደስታ ነው። ምላሽ የምሰጠው እርስዎ በመኾነዎ ነው። በዓለም ዋንጫው ይደሰቱ” ብለዋል።
ማካያ ማርክኤዝም በፈገግታ፣ “ይህ ለእኔ ይበቃኛል” ነው ያሉት።

ይህ የሃሳብ ልውውጥ በስፍራው ከነበሩት ታዳሚዎች ሞቅ ያለ ምላሽ አስገንኝቷል። ከጋዜጣዊ መግለጫው በኋላ ስካሎኒ ወደ አንጋፋው ጋዜጠኛ ተጠግተው በመተቃቀፍ እና አብረዋቸው ፎቶግራፍ በመነሳት ሌላ የማይረሳ ትዝታ ጥለው አልፈዋል።

የማካያ ማርክኤዝ ከዓለም ዋንጫ ጋር ያላቸው ቁርኝት ወደ ሰባት አስርት ዓመታት ገደማ ይጠጋል። እ.ኤ.አ. በ1934 በቦነስ አይረስ የተወለዱት ማርክኤዝ የጋዜጠኝነት ሥራቸውን የጀመሩት በ15 ዓመታቸው ራዲዮ ሪቫዳቪያ በተባለ የአርጀንቲና የሬዲዮ ጣቢያ ነበር።

ገና በ23 ዓመታቸው የ1958ቱን የዓለም ዋንጫ ለራዲዮ ቤልግራኖ ለመዘገብ ወደ ስዊድን ተጉዘዋል። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ የዘለቀውን ከእግር ኳስ ትልቁ ውድድር ጋር ያላቸውን ግንኙነት ጀመሩ።

የመጀመሪያው የዓለም ዋንጫ ሥራቸው ከ68 ዓመታት በፊት የነበረ ነው። ከስዊድኑ 1958 ጀምሮ በእያንዳንዱ የዓለም ዋንጫ ውድድሮች ላይ ዘገባዎችን ማቅረባቸውን በመቀጠል በአርጀንቲና የስፖርት ሚዲያ ውስጥ በጣም ከሚታወቁ ድምጾች አንዱ ለመኾን በቅተዋል።

እ.ኤ.አ. በ2022 በኳታር በተካሄደው የዓለም ዋንጫ ዓለም አቀፍ የስፖርት ጋዜጠኞች ማኅበር እና ፊፋ ማካያ ማርክኤዝን በወቅቱ 17 የዓለም ዋንጫዎችን በመዘገብ ከፍተኛውን የዓለም ዋንጫ የሸፈኑ ጋዜጠኛ በመኾን ክብረ ወሰን በማስመዝገባቸው ዕውቅና ተሰጥቷቸው ነበር።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የደቡብ አሜሪካ እግር ኳስ አሥተዳዳሪ አካል በ18ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ ሥራውን ሲጀምር ክብር ሰጥቷቸዋል። ሕይወታቸውን የእግር ኳስ ትውስታዎችን እና ስሜቶችን ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማሻገር የሰጡ ሰው በማለት ገልጿቸዋል።

የፊፋ ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖም በውድድሩ የመክፈቻ ሳምንት ማካያ ማርክኤዝን አድንቀዋል። ያስመዘገቡት ስኬት “በእውነት አስደናቂ” ሲሉ ጠርተውታል።

ማካያ ማርክኤዝ ከዓለም ዋንጫ ታሪካቸው ባሻገር፥ ከ1985 እስከ 2009 ታዋቂውን ፉትቦል ዴ ፕሪሜራ የተባለውን የቴሌቪዥን ፕሮግራም በመምራት እና የበርካታ ትውልዶችን የስፖርቱን ታሪክ በመዘገብ በአርጀንቲና እግር ኳስ ውስጥ ተፅዕኖ ፈጣሪ እና ታዋቂ ሰው ኾነው ቀጥለዋል።

የዓለም ዋንጫ ዘገባ ባለ ክብረወሰን ማካያ ማርክኤዝ አሁን ላይ 91 አመታቸው ላይ ይገኛሉ።

#አሚኮ_ዜና #ስፖርት

ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ኀይለኢየሱስ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here