ብዙ ባምላክ ተሰማዎችን ማፍራት የሚቻለው ለዳኝነት ሙያ ትልቅ ትኩረት ሲሰጥ ብቻ ነው” ኢንተርናሽናል ዳኛ ኃይለ ኢየሱስ ባዘዘው (ዶ.ር)

0
36

 

ባሕር ዳር: ሰኔ 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ እንደ አውሮፓዊያኑ የዘመን አቆጣጠር በ2018 እና በ2022 የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች ላይ ኢትዮጵያን ወክለው በዳኝነት ተሳትፈዋል፡፡

አሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ በጋራ በሚያዘጋጁት የ2026 ዓለም ዋንጫም ሰባት አፍሪካውያን ዳኞች ተመርጠዋል፤ ምንም እንኳን ሶማሊያዊው ዳኛ በአሜሪካ እገዳ ምክንያት በዕድላቸው ባይጠቀሙበትም፡፡

ሀገራችን በእግር ኳሱ ያጣችውን አሕጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተሳትፎዎች በዳኞቻችን ብቃት ማካካስ ችላ የነበረ ቢኾንም አሁን ላይ ግን ከዚህ ብቃታችንም ተንሸራትተናል፡፡

10 የአፍሪካ ሀገራት በዓለም ዋንጫው ድግስ ላይ ጥሪ የቀረበላቸው ሲኾን ሰባት የአፍሪካ ዳኞች የድግሱ የጥሪ ካርድ ደርሷቸዋል፡፡

ሙስጠፋ ጎርባል (አልጄሪያ)፣ አሚን ሞሐመድ (ግብጽ)፣ ፒየር አቾ (ጋቦን)፣ ጃላል ጃርድ (ሞሮኮ)፣ ዳሃኔ ቤይዳ (ሞሪታኒያ)፣ ኦቦንጊሴ ቶም (ደቡብ አፍሪካ) እና ኦማር አርታር (ሶማሊያ) የጥሪው ካርድ የደረሳቸው አፍሪካዊያን ኢንተርናሽናል ዳኞች ናቸው፡፡

ኢንተርናሽናል ዳኛ ኃይለኢየሱስ ባዘዘው (ዶ.ር) በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ዳኝነት እድገት እያሳየ አይደለም፤ ለዚህም ማሳያ የሚኾነው የሀገራችን ዳኞች በአፍሪካም ኾነ በዓለም የእግር ኳስ መድረኮች ላይ አለመታየታቸው ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በአፍሪካ ከ34 ሀገራት በላይ ተዘዋውረው ትላልቅ ጨዋታዎችን የዳኙት ዶክተር ኃይለኢየሱስ በሀገራችን ዳኞችን ለትልቅ መድረክ ለማብቃት ወይም ትላልቅ ጨዋታዎችን እንዲዳኙ ለማስቻል በዕቅድ ተይዘው የሚሠሩ ሥራዎች አነስተኛ ናቸው ይላሉ፡፡

ዳኞች ራሳቸውን በአካል ብቃት፣ በሕግ ዕውቀት፣ በሕግ አተገባበር እና በሥነ ልቦና በአግባቡ አለመዘጋጀታቸው እንዲሁም እግር ኳስን የሚመሩት አካላት ዳኝነቱንም ልክ እንደ እግር ኳሱ ማደግ አለበት ብለው አለመሥራታቸው ሌላኛው ውስንነት መኾኑን ጠቅሰዋል፡፡

የሀገራችን የእግር ኳስ ፌዴሬሽን በእግር ኳስ ጨዋታም ኾነ በዳኝነቱ ዙሪያ ብዙ ሥራዎችን መሥራት እንደሚጠበቅበት የገለጹት ኢንተርናሽናል ዳኛው መጓተት እና የቡድንተኝነት ስሜት ከሙያው አካባቢ መራቅ እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡

የዳኞች ግልጽ ስህተት ወይም አድልኦ ፈጻሚነት በወቅቱ እና በሕግ አግባብ መታረም ካልቻለ ዳኞችን የጠቀምናቸው ቢመስለንም እየጎዳናቸው መኾኑ መታወቅ አለበትም ብለዋል፡፡

የሶማሊያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሶማሊያዊው ኢንተርናሽናል ዳኛ ኦማር አርታን ላይ ብዙ ጊዜ ወስደው እና በትኩረት በመሥራታቸው ዳኛው ምሥራቅ አፍሪካን በዓለም ዋንጫው በዳኝነት እንዲወክሉ አስችለዋል ያሉት ኃይለኢየሱስ በኛ ሀገር ሰባት ኢንተርናሽናል ዳኞች ቢኖሩም ከፌዴራል ዳኞች በተለየ የሚደረግላቸው ድጋፍም ኾነ ክትትል ባለመኖሩ እድገታቸው ባለበት ተገድቧልም ብለዋል፡፡

ዶክተር ኃይለኢየሱስ የዳኝነት ሙያ በሀገር ውስጥ ብቻ ከታጠረ ጥሩ ገቢ የሚያስገኝ አይደለም ያሉ ሲኾን ራስን ከፍ ባለ መድረክ ማሳተፍ ከተቻለ ግን ለሙያው ተገቢ የኾነ ክፍያን ማግኘት ይቻላል ነው ያሉት፡፡

በቀጣይ ጊዜያት “ብዙ ባምላክ ተሰማዎችን ማፍራት የሚቻለው ለዳኝነት ሙያ ትልቅ ትኩረት ሲሰጠው ነው” ብለዋል። የዳኞችን አቅም ለማሳደግም በካፍ እና በፊፋ በሚሰጡ የዳኝነት ሥልጠናዎችም ኾነ የአቅም ግንባታዎች ላይ ኢትዮጵያዊ ዳኞችን ማሳተፍ የግድ ይለናል ብለዋል።

ከሁሉም በላይ ግን የዳኝነት ሥልጠና መጀመር ያለበት በፕሮጀክቶች መኾን እንዳለበትም ኢንተርናሽናል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው (ዶ.ር) አሳስበዋል፡፡

በእሱባለው ይርጋ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here