1ኛው የኢትዮጵያ 10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር በባሕር ዳር ከተማ ይካሄዳል።

0
38

 

​አዲስ አበባ: ሰኔ 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የፊታችን እሑድ ሰኔ 07/2018 ዓ.ም 1ኛው የኢትዮጵያ 10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር በባሕር ዳር ከተማ ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በሰጠው መግለጫ ለውድድሩ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ገልጿል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ መሐሪ ነጋሽ የፌዴሬሽኑ ቴክኒክ ባለሙያዎች ቀደም ብለው ወደ ባሕር ዳር በማቅናት አስፈላጊውን ሥራ እያከናወኑ መኾኑን ተናግረዋል።

በውድድሩ የግል ተወዳዳሪዎችን ጨምሮ ከ6 ክለቦች የተውጣጡ 91 አትሌቶች ተሳታፊ ይኾናሉ።

በውድድሩ ከ1ኛ እስከ 8ኛ ለሚወጡ አትሌቶች የገንዘብ ሽልማት እንደሚበረከት ፌዴሬሽኑ በመግለጫው ጠቅሷል።

ውድድሩ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በዓለማቀፍ የውድድር ሕግ እና በፌዴሬሽኑ ደንብ ይመራል ሲሉ የተናገሩት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የውድድር እና ተሳትፎ ዳይሬክተር ተወካይ ጊዜ አድነው ናቸው።

መነሻ እና መድረሻውን ርእሰ መሥተዳድር ጽሕፈት ቤት አካባቢ በማድረግ የሚካሄደው 1ኛው የኢትዮጵያ 10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር እሑድ ሰኔ 7/2018 ዓ.ም ከጠዋቱ 12:00 ጀምሮ ይካሄዳል ብለዋል።

ውድድሩ በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) በቀጥታ ይተላለፋል።

#አሚኮ_ዜና #ስፖርት_አትሌቲክስ_ባሕር_ዳር #አማራ_ክልል_ኢትዮጵያ🇪🇹

ዘጋቢ፦ ባዘዘው መኮንን

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here