ከሳምንት በፊት በስፔን 2ኛ ዲቪዚዮን ቴነሪፌና አንዶራ ክለቦች ባደረጉት ጨዋታ አሳዛኝ ነገር መከሰቱ ይታወሳል።
በጨዋታው ማብቂያ አካባቢ የቴነሪፌው አጥቂ ጀሱስ ዲ ሚጉኤል ኳስ ለማግኘት በሚጥርበት ወቅት የአንዶራው ግብ ጠባቂ ጀሱስ አዎኖ የግብ ክልሉን ለቆ በመውጣት በፈጠሩት ግጭት ዲ ሚጉኤል ከባድ ጉዳት ደርሶበታል።
ስፔናዊው አጥቂ በአፋጣኝ ወደ ሆስፒታል ቢወሰድም ሊተርፍ ባለመቻሉ ህይወቱ አልፏል።
የስፔን ፖሊስ ጉዳዩ ሆን ተብሎ ነፍስ ከማጥፋት ድርጊት ጋር የሚያያዝ መሆን አለመሆኑን የማጣራት ምርመራ አድርጎ የነበረ ቢሆንም ድርጊቱ ከስፖርታዊ ንክኪና ግጭት ጋር ብቻ የተያያዘ ኾኖ በመገኘቱ የስፔን እግርኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴ በግብ ጠባቂው ላይ የ12 ጨዋታዎች ቅጣት አስተላልፎበታል።
ይህ የጨዋታ ቅጣት ውሳኔ በስፔን እግርኳስ የመጨረሻውና ከፍተኛው መኾኑ ታውቋል።
በተጨማሪም የጨዋታው ቀሪ ደቂቃዎች ድጋሚ እንዳይካሄዱና ድርጊቱ እስኪከሰት ድረስ የነበረው የ2 ለ 2 አቻ ውጤት ባለበት እንዲፀድቅ ተወስኗል።
ያም ኾኖ የ25 ዓመቱ ኢኳቶሪያል ጊኒያዊ ግብ ጠባቂ ጀሱስ አዎኖ የዲ ሚጉኤል ህልፈት ከተሰማ በኋላ ላለፉት 10 ቀናት ከፍተኛ የመንፈስ ጭንቀትና ስቃይ ውስጥ እንደሚገኝ ቢቢሲ ዘግቧል።
ይህንን ተከትሎ ዳግም ወደ እግርኳስ መመለሱ አጠራጣሪ እንደሆነ የአንዶራው አሰልጣኝ ካርሎስ ማንሶ ተናግረዋል።
#አሚኮ #ስፖርት🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ኅዳር_05_2019_ዓ_ም
በኃይሌ አበራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!



