ዐይን ያየው የአፍሪካ ምልክቱን ሰንደቅዓላማ፤ ጆሮ የሰማው የእናት ኢትዮጵያን መዝሙር ነበር።

0
22
እግር ኳስ በተለይም የብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች በሜዳ ላይ በሚደረግ የ90 ደቂቃ የኳስ ፍልሚያ እና የደጋፊዎች የኳስ ፍቅር የሚታይበት ትዕይንት ብቻ ሳይኾን ሰፊ ማኅበራዊ እና ሥነ-ልቦናዊ እሴት ያለው ታላቅ የሕዝቦች መተሣሠሪያ መድረክም ነው።
በተንጣለለው ስታዲየም ውስጥ ጨዋታው በሚጀመርበት ቅፅበት የሰዎች የሃሳብ፣ የማኅበራዊ ደረጃ፣ የዕድሜም ኾነ ሌሎች የማንነት ልዩነቶች በሙሉ ወደ ጎን ገሸሽ ይደረጋሉ። ሁሉም ለአንድ ዓላማ ይሰለፋሉ። አንድም በኳስ ለመዝናናት አልያም የራስን ብሔራዊ ቡድን ለመደገፍ።
ይህም እግር ኳስን ሰዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአንድ ስሜት፣ በአንድ ዜማ እና በአንድ ዓላማ የሚቆሙበትን ልዩ መድረክ የሚፈጥር ነው ያስብለዋል። በአንድ የብሔራዊ ቡድን ማልያ ሥር የሚሠበሠቡ ዜጎች ሁሉ “እኔ” የሚለውን ግለሰባዊ ማንነት ትተው “እኛ” በሚል የጋራ ሀገራዊ ማንነት ውስጥ እንዲዋሃዱ የሚያደርግ መድረክ ነውም ያሰኘዋል።
ታዲያ በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ይህ ጥልቅ ስሜት በገሃድ የሚስተናገድበት መድረክ አልነበረም። ሕዝቡ ብሔራዊ ቡድኑን በአካል አግኝቶ የሚደግፍበት ዕድልም አልነበረውም። ይህ የኾነውም ኢትዮጵያ የካፍን መስፈርቶች የሚያሟላ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ስላልነበራት መኾኑ ይታወቃል። ይህም በሕዝቡ እና በእግር ኳስ ወዳዱ ማኅበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ቁጭት ሲፈጥር ነበር።
ከዓመታት ጥበቃ በኋላም በከፍተኛ ጥንቃቄ እና ጥራት ተገንብቶ በተጠናቀቀው የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ቁጭቱ ነበር ኾኗል።
ዋልያዎቹም የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታቸውን በደጋፊያቸው ፊት በውብ ሀገራዊ ኅብረ ዜማ እና በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ አርማ ታጅበው ማካሄድ ቻሉ።
ይህ ዕለት ለዋልያዎቹ እና ለደጋፊያቸው አልፎም ለተጋጣሚው የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን ከልብ የማይጠፋ ማኅተም የተፃፈበትም ነበር።
በውኃ ሰማያዊ እና ነጭ ቀለም ያሸበረቀው የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ለ90 ደቂቃ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀዩን ሰንደቅዓላማ በለበሱ እና በልባቸው ባነገቡ ደጋፊዎች ተሞልቶ ነበር።
ከሁሉም በላይ በስታዲየሙ ውስጥ ማዶ እና ማዶ የተቀመጡት የዋሊያዎቹ ደጋፊዎች ጥልቅ ሀገራዊ ዝማሬዎችን በቅብብል ከፍ አድርገው በማሰማት ለሀገር እንዲሁም ለብሔራዊ ቡድኑ ያላቸውን ክብር አሳይተዋል።
ዋልያዎቹ አረንጓዴ በለበሰው ውብ ሜዳ በተሰጣቸው እግር ኳሳዊ ክሕሎት ለሀገራቸው ክብር ሲዋደቁ ደጋፊው አንዴ ከመቀመጫው በመነሳት፤ ሌላ ጊዜ እጅ ለእጅ ተያይዞ እንዲያም ሲል ተቃቅፎ ወደኋላ በመዞር “ውብ ሀገሬ ውብ ሀገሬ፤በአንቺ እኮ ነው መከበሬ” በማለት የደበዘዘ የሚመስለውን ነገር ግን የተዳፈነውን ኢትዮጵያዊነት ገላልጦ ሲያፈካው ዓለም በአግራሞት ተመልክቷል።
በስታዲየሙ ከኳስ ባሻገር በደም የተከበረ ነጻ ሀገር እና ሕዝብነትም ተንጸባርቋል። “ተከብረሽ የኖርሽው በአባቶቻችን ደም በአባቶቻችን ደም…እናት ኢትዮጵያ የደፈረሽ ይውደም” በማለት ሲያዜሙ ሰውነትን አንዳች ነገር ይነዝር ነበር።
በጥቅሉ በስታዲየሙ ዐይን ያየው አርንጓዴ ቢጫ ቀዩን ሰንደቅዓላማ፤ ጆሮ የሰማው እናት ኢትዮጵያን ነበር። ይህ ታዲያ ጨዋታውን ለመመልከት ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም በተገኙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ እንግዳ ነገር ነበር። የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች እና የአማራ ክልል ሕዝብ ላሳየው ሀገራዊ ስሜትም ከፍተኛ አድናቆት የለገሱት በርካታ ናቸው።
ጨዋታው የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን ማስተናገድ መጀመሩ በስፖርት መሠረተ ልማት ስኬት ብቻ የሚታይ አይደለም። ስታዲየሙ ከእንግዲህ ወዲህ የኢትዮጵያዊነት እሴቶች በደመቀ ሁኔታ የሚንጸባረቁበት፣ የሚታደሱበት እና ለዓለም የሚታዩበት ሕያው ዓደባባይ ኾኖ እንደሚቀጥል ጥርጥር የለውም።
በአድኖ ማርቆስ
‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here