“ባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየምን በድጋሚ ወደ ሥራ የሚያስገባው ታሪካዊው ጨዋታ”

0
145

 

የኢትዮጵያ ወንዶች እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን ከሴኔጋል አቻው ጋር መስከረም 19/2019 ዓ.ም በባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታውን ያደርጋል።

ጨዋታውን በስኬት ለማስሄድ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታውቋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል እና የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር አበበ ውቤ ጨዋታው ለክልሉ ትልቅ ዕድል ይዞ የሚመጣ ነው ብለዋል። ይህ ጨዋታ አዲስ የገቢ ምንጭ ከመፍጠሩ ባሻገር በአካባቢው አስተማማኝ ሰላም መኖሩን በተግባር የሚያረጋግጥ እና ስታዲየሙን በድጋሚ ወደ ሥራ የሚያስገባ ታሪካዊ ክስተት እንደኾነ ነው የተናገሩት።

ለጨዋታው ስኬት ዝግጅቱ በተቀናጀ መንገድ እየተመራ መኾኑንም አስታውቀዋል። ለጸጥታ አካላት እና ለወጣቶች ተገቢው ሥልጠና እና ግንዛቤ መሰጠቱንም ገልጸዋል። የክልሉ የሥራ ኀላፊዎችም ትኩረታቸውን ለጨዋታው በማድረግ በከፍተኛ ቅንጅት ሌት ከቀን እየሠሩ ነው ብለዋል።

የሕዝቡ እና የወጣቶች ተሳትፎ ከፍተኛ መኾኑን የገለጹት ምክትል ኮሚሽነሩ ማኅበረሰቡ የሥራው ዋነኛ ባለቤት መኾን አለበት ነው ያሉት። በመኾኑም ጨዋታውን ለመታደም ለሚመጡ እንግዶች የባሕር ዳርን እና የሕዝቧን የታወቀ እንግዳ ተቀባይነት በተግባር ሊያሳዩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ጨዋታው ሰላማዊ እና ፍቅር የተሞላበት ኾኖ እንዲጠናቀቅ የወጣቶች እና የመላው ማኅበረሰብ ንቁ ተሳትፎ፣ እገዛ እና ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።

የባሕር ዳር ከተማ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ዋለልኝ ቢምረው በባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ለሚካሄደው የእግር ኳስ ጨዋታ የካፍ (CAF) መስፈርትን ባሟላ መልኩ ከፌዴራል፣ ከክልል እና ከወጣቶች ጋር በመቀናጀት በቂ የጸጥታ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

የካፍ የደኅንነት ኀላፊዎች ባሉበት ስታዲየሙ ማስተናገድ የሚችል እና በቂ የጸጥታ ኃይል ያለው መኾኑ መረጋገጡንም ጠቁመዋል። ዝግጅቱ ቀጣይነት ላላቸው ጨዋታዎች ጭምር የሚያገለግል በመኾኑ የከተማዋ ነዋሪዎች ጸጥታን ማስከበር ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ጠይቀዋል።

#አሚኮ #Football #Ethiopia🇪🇹

#ባሕር_ዳር #መስከረም_12_2019_ዓ_ም

ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here