በጎንደር ከተማ አሥተዳደር የወርልድ ቴኳንዶ፣ የኢንተርናሽናል ቴኳንዶ፣ የውሹ እና የቦክስ ውድድሮች የመክፈቻ መርሐ ግብር ተካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ የተገኙት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ባሕል ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ማርያማዊት ካሳሁን በአራቱም ዘርፎች የተጀመረው ስፖርታዊ ውድድሩ ከ18 የስፖርት ማዕከላት የተወጣጡ እና ከ200 በላይ ታዳጊዎች የሚሳተፉበት ነው ብለዋል።
በስፖርት ዘርፉ የሚታዩ ተሞክሮዎችን ለማስፋት አላማ ያደረገው ውድድሩ ለተከታታይ ሰባት ቀናት የሚቀጥል መኾኑንም ተናግረዋል። ውድድሩ በሁሉም ዘርፎች የተሻሉ ስፖርተኞችን በመለየት በቀጣይ ለሚደረጉ ዞናዊ እና ክልላዊ ውድድሮች አስተዋጽኦ አለው ነው ያሉት።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ የሥልጠና እና ውድድር ባለሙያው እንዳልካቸው ሢሳይ ውድድሩ የወጣቶችን የእርስ በርስ ግንኙነትን በማጠናከር የልምድ ልውውጥ ለማድርግ የሚያስችል መኾኑን ገልጸዋል።
ውድደሩ ወጣቶች ስፖርት ላይ ያላቸውን ተሳትፎ እንዲያጠናክሩ ከማድረግ ባሻገር ከአልባሌ ቦታ ታቅበው ጊዜያቸውን እንዲያሳልፉ እንደሚረዳቸው ያሳወቁት ደግሞ ሀሳባቸውን የሰጡ ተወዳዳሪዎች ናቸው።
ከአስተያየት ሰጭዎቹ መካከል የወርልድ ቴኳንዶ ሠልጣኝ ሕይወት አያና የውድድሩ መዘጋጀት ከውድድር ባለፈ ለስፖርተኞች ጤና መጠበቅ ያለው ጥቅም ከፍተኛ መኾኑን ተናግራለች። ውድድሩ ለነገ መሠረት የሚጥል መኾኑንም አንስታለች።
በማርታ አዱኛ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!



